ፕሬዚዳንት ማክሮን ብሄራዊ ምክር ቤቱን ለመምራት ከግራ ዘመም ፖለቲከኞች ጋር ሊፋለሙ ነው

ታትሟል

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በድጋሚ በፕሬዚዳንትነት ከተመረጡ ሁለት ወራት እንኳን አልሞላቸውም ነገር ግን ማሻሻያዎቻቸውን እንዳይተገብሩ ሊያግደው የሚችል ፈታኝ ምርጫ ውስጥ ገብተዋል።

ፈረንሳያውያን ብሄራዊ ምክር ቤቱን ማን እንደሚቆጣጠር ለመወሰን የሚያስችለውን ድምፅ ለመስጠት በዛሬው ዕለት ወደየምርጫ ጣቢያዎች ያቀናሉ።

ፕሬዚዳንት ማክሮን በሚያዝያ ወር ቀኝ አክራሪ የሆነውን ሃይል ቢያሸንፉም በአሁኑ ወቅት የገጠማቸውን የግራ ዘመም ፖለቲከኞች ጥምረት ማሸነፍ ሊከብዳቸውም እንደሚችል እየተነገረ ነው።

የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለምን የሚከተሉት ዣን ሉክ ሜሌንቾን ከማክሮን ጋር በጠበበ ውጤት ያጠናቀቀውን የግራ አረንጓዴ ጥምረት ይመራሉ።

እራሳቸውን ኑፔስ ብለው የሚጠሩት ጥምረት ለከባቢ ጥንቃቄ እና ማህበራዊ ደህንነት እንታገላለን የሚሉ ሲሆን አስተያየቶችም እንደሚያሳዩት ፕሬዚዳንቱ የሚያስፈልጋቸውን አብላጫ ድምፅ ወይም 289 ወንበሮችን ለማግኘት ይገታቸዋል የሚል ነው።

 ማዕከላዊ ፖለቲካ እከተላለሁ የሚሉት ፕሬዚዳንት ማክሮን ጥምረቱ የኮሙዩኒስቶች፣ ሶሺያሊስቶች፣ ግራ ዘመም አክራሪ ሜሌንቾኒስቶችና “ጊዜያዊ ጋብቻ” ነው እንደሆነ አድርገው ነው የሚገልጿቸው ።

ነገር ግን ኑፔስ ያለውን የዋጋ ግሽበት እንታገላለን፣ የጡረታን ዕድሜን ለማውረድና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ቃል በመግባት መራጮችን ማሰባሰብ ችለዋል። በተለይም ለአረንጓዴ ልማት የሚታገሉ አመራሮች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ፕሬዚዳንት ማክሮን ብዙም እንዳልሰሩ በመግለፅ ይደግፏቸዋል።

የዛሬው ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሁለት እጩዎች መካከል የሚደረግ ፉክክር ሲሆን ግማሹም ሁለቱን ትልልቅ ጥምረት ያካትታል። በፕሬዚዳንት ማክሮን መንግሥት ውስጥ ያሉ በርካታ ሚኒስትሮች ወንበራቸውንና ስልጣናቸውን ለማስጠበቅ እየተፋለሙ ነው።

ፕሬዚዳንት ማክሮን አብላጫ ድምፅ የሚባለውን 289 ወንበሮች ማግኘት ካልቻሉ የጡረታ ዕድሜን ከፍ ማድረግ፣ የግብር ቅነሳ እና ጥቅማ ጥቅሞች ማሻሻያ የመሳሰሉ ፖሊሲ ለውጦችን ለመግፋት የሌሎች ፓርቲ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።

በአሁኑ ወቅ ያሉ የህዝብ አስተያየት እንደሚጠቁሙት ኢንሰምብል የተባለው ፓርቲ 225-305 መቀመጫዎችን እንዲሁም ኑፔስ 140- 200 ወንበሮችን እንደሚያሸንፉ ነው።

በያዝነው ሳምነት አርብ በነበረው የድምፅ ማሰባሰብ ቅስቀሳ የኑፔስ ቃል አቀባይ ኢያን ብሮሳት በፓሪስ ላሉ ደጋፊዎቻቸው ባስተላለፉት መልዕክት  “ግራ ዘመም ርዕዮተ አለምና የአረንጓዴ ልማት ፖለቲከኞች ሊሰባሰቡ ይችላሉ ብለው አልጠበቁም ነበር። ቢሰባሰቡ ትርምስ እና ጥፋት ይመጣል ብለው ነበር የሚጠብቁት። በአሁኑ ወቅት ያለው ትርምስ ኢኮኖሚያዊ ነው፤ የምግብ ዋጋ መናርና አስር ሚሊዮን ሰዎች በድህነት ውስጥ መኖር ” ብለዋል።