በቱርክ ርዕደ መሬት የነፍስ አድን ሥራው በከባድ ዝናብ ተስተጓጎለ

ርዕደ መሬት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በደቡብ-ምስራቅ ቱርክ ከደረሰው ከባድ ርዕደ መሬት በሕይወት የተረፉ ሰዎችን ለማግኘት ላይ ታች ሲሉ የነበሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች በረዶ በቀላቀለ ከባድ ዝናብ እየተፈተኑ መሆናቸው ተገለጸ።

ሰኞ ረፋድ በቱርክ እና በሶሪያ ድንበር ላይ በደረሰው ርዕደ መሬት ከ4 ሺህ 300 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች በርካታ ተጎጂዎችን እያገኙ መሆናቸውን ከግምት በማስገባት የጉዳቱ መጠን ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።

በአደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ በርካታ ሰዎች ወደ መኖሪያ ህንፃዎቻቸው ለመመለስ መፍራታቸውም ተነግሯል።

የአሜሪካው የጂኦሎጂካል ሰርቬይ እንደገለጸው ከሆነ በሬክተር ስኬል 7.8 የተመዘገበው ርዕደ መሬት በጋዚያንቴፕ ከተማ አቅራቢያ በ17.9 ኪሜ ጥልቀት ውስጥ ተከስቷል።

የርዕደ መሬት ተመራማሪዎች እንደሚሉት በቱርክ ቢያንስ 2,921 ሰዎችን ከገደለው አደጋም የአሁኑ ትልቁ ነው። ከአደጋው የተረፉ ሰዎች መንቀጥቀጡ ለመቆም ሁለት ደቂቃ እንደፈጀበት ተናግረዋል።

በኋላ ላይ የተነሳው የመሬት መንቀጥቀጥ 7.5 መጠን ያለው ሲሆን የተከሰተውም በካህራማንማራስ ግዛት በኤልቢስታን አውራጃ ነበር።

ከርዕደ መሬቱ በኋላም በነበረው መንቀጠቀጥ ሳይበገሩ አንዳንድ የነፍስ አድን ሠራተኞች በህይወት የተረፉ ሰዎችን ለማዳን በባዶ እጃቸው ጭምር ፍርስራሾችን ቆፍረዋል።

በቱርኳ ኦስማኒዬ ከተማ አቅራቢያ ከደረሰው አደጋ በህይወት የተረፉትን ለማዳን የሚደረገውን ርብርብ እየጣለ የሚገኘው ዝናብ ለነፍስ አድን ሠራተኞች ፈተና እንደሆነባቸው ታውቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቅዝቃዜው እና ከዝናቡ በተጨማሪ ከተማዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎትም አጥታ ነበር።

ከባድ ቅዝቃዜ ቢኖርም የአንድ ቤተሰብ አባላት ከደረሰው ጉዳት የተነሳ ሕንጻ ሊፈርስ ይችላል በሚል ጎዳና ላይ መሰባሰብን መርጠዋል።

ድህረ መንቀጥቀጥ በተሰማቸው ቁጥር የቤተሰቡ አባላት ወደ መሀል መንገድ ይጠጋሉ።

በከተማዋ የሚገኝ አንድ የሆቴል ባለቤት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከነበሯቸው 14 እንግዶች የተገኙት ሰባት ብቻ ናቸው።

በርካታ ሃገራት ባለሙያዎችን፣ አነፍናፊ ውሻዎችን እና ድጋፍ ሰጪ መሳሪያዎችን ጨምሮ የነፍስ አድን ጥረቶችን ለመርዳት ድጋፍ እየላኩ ነው።

ርዕደ መሬቱ በመላው ቱርክ በሚገኙ ሦስት አየር ማረፊያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ ለዕርዳታ አቅርቦት ፈተና ፈጥሯል።

በቱርክ ድንበር ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች በሚኖሩባት ሶሪያ ቢያንስ 1,400 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።

ትውልደ እንግሊዛዊው ዶክተር ሻጁል ኢስላም በሰሜን ሶሪያ በምትገኘው ኢድሊብ በአል-ሺፋ ሆስፒታል ላለፉት ሰባት ዓመታት አገልግሏል። በሆስፒታሉ የገጠመው እስካሁን ታይቶ በማያውቀው መልኩ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ሆስፒታላችን ሞልቷል። አሁን በሆስፒታሉ ውስጥ ከ300-400 የሚደርሱ ህሙማን አሉን... በትክክል ለመግለጽ በአንድ አልጋ ከሁለት እስከ ሦስት ታማሚዎች አሉን" ብሏል።

በጽኑ ህሙማን ክፍል ከ40-45 በጠና የታመሙ ሕሙማንን እየተንከባከብን ነበር ሲል ተናግሯል። “ከሕሙማንን ላይ ኦክስጅን እየነቀልኩ በሕይወት የመትረፍ እድል ላላቸው ሌሎች ሕመምተኞች ለመስጠት ተገድጃለሁ። በሆስፒታሉ መግቢያ ሆነን የትኞቹን ታካሚዎች ለማዳን እንደምንሞክር እየወሰንን ነው” ብሏል።

የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ዓለም አቀፍ የእርዳታ ጥሪን ተከትሎ 45 ሃገራት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአደጋው ከተጎዱት ቤተሰቦች መካከል አብዛኛዎቹ “ቀድሞውንም ፈታኝ በሆነባቸው አካባቢዎች የሚገኙ በመሆናቸው ሰብዓዊ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ዓለም አቀፍ ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የአውሮፓ ህብረት ወደ ቱርክ የነፍስ አድን ቡድኖችን እየላከ ሲሆን የኔዘርላንድስ እና የሮማኒያ የነፍስ አድን ሠራተኞች ደግሞ ጉዞ መጀመራቸው ተገልጿል። እንግሊዝ 76 ባለሙያዎችን፣ መሳሪያዎችን እና አነፍናፊ ውሾችን እንደምትልክ አስታውቃለች።

ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ እስራኤል እና አሜሪካም ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። ኢራንን ጨምሮ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለቱርክ እና ለሶሪያ እርዳታ ሰጥተዋል።

ቱርክ ርዕደ መሬት በሚከሰትባቸው ዞኖች ውስጥ ትገኛለች።

እአአ በ1999 በሰሜን-ምዕራብ በደረሰ ርዕደ መሬት ከ17,000 በላይ ሰዎችን ሞተዋል። በ1939 ደግሞ በምስራቃዊ የኤርዚንካን ግዛት 33,000 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

የአሁኑ ርዕደ መሬት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ እስከ ቆጵሮስ፣ ሊባኖስና እስራኤል ድረስ ተሰምቷል።