የአሜሪካ ጦር የተሰወረበትን ኤፍ- 35 የጦር ጄት ለመፈለግ የሕዝብን እርዳታ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, PA MEDIA
የአሜሪካ ጦር አብራሪው በፓራሹት ከወረደ በኋላ የተሰወረበትን ዘመናዊና ውድ የጦር ጄት ያለበትን ለማወቅ የሕዝብ እርዳታን ጠየቀ።
ጄቱ የጠፋው የአሜሪካ ደቡባዊ ግዛት በሆነችው ደቡብ ካሮላይና እየበረረ በነበረበት ወቅት ነበር።
እሑድ ዕለት ከሰዓት በኋላ የጠፋውን የጦር አውሮፕላን ሲያበር የነበረው ስሙ ያልተገለጸው አብራሪ ፓራሹት በመጠቀም ከጄቱ ውስጥ ለመውረድ የቻለ ሲሆን በሆስፒታል ውስጥም በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።
እስካሁን የክስተቱ መንስኤ ግልጽ ባይሆንም ባለሥልጣናት የጦር አውሮፕላኑ ድንገተኛ ችግር አጋጥሞት እንደነበር ተናግረዋል።
ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ኤፍ-35ቢን ለመፈለግም በቻርለስተን ሰሜናዊ ክፍል በሚገኙ ሁለት ሐይቆች አካባቢ ትኩረት ተደርጓል።
ጄቱ ለመጨረሻ ጊዜ የታየበትን ሞልትሪ ሐይቅ እና ማሪዮን ሐይቅ አካባቢን መሠረት በማድረግም በፌደራል አቪየሽን ተቆጣጣሪዎች ፍለጋው እየተካሄደ ነው።
በሰሜን ቻርለስተን የሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር፣ ጆይንት ቤዝ ቻርለስተን በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ለሕዝቡ የእርዳታ ጥሪን አቅርቧል።
“በሚደረገው ጥረት ሕዝቡ ከወታደራዊ እና ሲቪል ባለሥልጣናት ጋር እንዲተባበር ተጠይቋል” ሲል መልዕክት አስተላልፏል።
የፍለጋ ቡድኖቹን የሚረዳ መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው ለኦፕሬሽን ማዕከሉ ጥቆማ እንዲሰጥም አበረታቷል።
የአሜሪካ ጦር ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫም፣ አሁን ላይ ስለ ክስተቱ ያለው መረጃ ውስን መሆኑን ገልጾ፣ ተጨማሪ መረጃ ለመሰብሰብ እየሞከረ መሆኑን ገልጿል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ማጂ ሜላኔ ሳሊናስ በበኩላቸው ከተሰወረው ጄት ጋር በተመሳሳይ ሰዓት ይበር ነበር የተባለው ሁለተኛው ኤፍ- 35 ጄት በቻርለስተን ወደሚገኘው ማረፊያው በሰላም መመለሱን ለአሶሺየትድ ፕረስ ተናግረዋል።
ኤፍ-35 ጄት ሎክሂድ ማርቲን በተሰኘ የአሜሪካ ኤሮስፔስ ድርጅት የተሰራ ሲሆን እያንዳንዱ 100 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳለው ይገመታል። ይህ ጄት በዓለማችን ካሉ እጅግ ዘመናዊ ተዋጊ ጄቶች መካከልም አንዱ ነው።
ኤፍ -35 በዓለም ላይ ካሉ የጦር መሣሪያዎች በዓይነቱ በጣም ትልቁና ውድ የሆነ ጄት ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ 2018 በደቡብ ካሮላይና ግዛት የመከስከስ አደጋ ካጋጠመ በኋላ የአሜሪካ ጦር ኤፍ-35 ተዋጊ ጀቶቹን በጊዜያዊነት ከበረራ አግዶ እንደነበር ይታወሳል።












