አሜሪካ ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሸከርካሪን በስቶ የሚገባ የታንክ ጥይት ለዩክሬን ልትሰጥ ነው

ታንክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ዩናይትድ ስቴትስ ዩራኒየም ተሟጦ የወጣለት የታንክ ጠይት በእርዳታ መልክት ለዩክሬን ልትሰጥ እንደሆነ ይፋ አደረገች።

እርዳታው አሜሪካ ለዩክሬን ሰብዓዊ እና ወታደራዊ እርዳታ ይሆናል ብላ ከመደበችው 1 ቢሊዮን ዶላር መካከል አንዱ ነው።

አሜሪካ አብራምስ የተባሉት ታንኮች የሚውጡት ይህ አወዛጋቢና ብረት ለበስ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በስቶ የሚገባ ጥይት ለዩክሬን መሰጠቷ ትክክል አይደለም ስትል ሞስኮ ተቃውሞ አሰምታለች።

የአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍ ዜና የተሰማው ዩክሬን ሩሲያ በወሰደችው የሚሳዔል ጥቃት 17 ሰዎች ተገድለውብኛል የሚል ሪፖርት ካወጣች በኋላ ነው።

የሩሲያ የሚሳዔል ጥቃት ከተሰማ በኋላ ረቡዕ ሌሊት በሩሲያዋ ሮስቶቭ-ኦን-ዶን ከተማ ከዩክሬን የተተኮሰ ነው የተባለ የድሮን ጥቃት ተዘግቧል።

ማሕበራዊ ሚድያ ላይ የተለጠፉ ያልተጣሩ ምስሎች በማዕከላዊ ሮስቶቭ ፍንዳታ እንዳለ ያሳያሉ።

የሮስቶቭ ገዥ ቫሲሊ ጎሉቤቭ በበኩላቸው አንድ ሰው መለስተኛ ጉዳት ደርሶበታል፤ በርካታ ተሽከርካሪዎችም እንዲሁ ወድመዋል ብለዋል።

አክለው ሁለት ድሮኖች በደቡባዊ የሩሲያ ክፍል የምትገኘውን ከተማ ዒላማ አድርገው ቢመጡም ሁለቱም ተመተው ወድቀዋል ሲሉ ገልጠዋል።

የሞስኮው ከንቲባ ሰርጌይ ሶብያኒን በበኩላቸው አንድ ድሮን የራሜንሰኮይ ከተማን ዒላማ አድርጎ ቢመጣም ተመትቶ መውደቁንና ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረሱን ተናግረዋል።

ከሩሲያ የሚወጡ ዘገባዎችን ትክክለኛነት በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልተቻለም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት አንተኒ ብሊንከን ወደ ኪይቭ አቅንተው ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ነው እርዳታው ይፋ የሆነው።

ባለ 120 ሚሊ ሜትር የታንክ ጥይት እና 175 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሣሪያ እርዳታ ኤም1 አብራምስ ለተሰኙት ታንኮች የሚሆን ሲሆን በያዝነው የአውሮፓዊያኑ ዓመት መገባደጃ ዩከሬን ይደርሳል።

ዲፕሌትድ ዩራኒየም የሚባለው ራድዮአክቲቭ ንጥረ-ነገር ሙሉ በሙሉ ባይሆን በአብዛኛው ተፍቆ ከተፈጥራዊ ዩራኒየም የሚሠራ ነው።

ዩራኒየም ማለት በጣም ክብደት ያለው ብረት ነው። ይህ ማለት ዲፕሌት አሊያም የተሟጠጠ የተባለው ዩራኒየም ለታንክ ጥቅም እንዲውል ተደርጎ ይሠራል ማለት ነው።

አልፎም በጥይቶች ጫፍ ላይ፤ በሞርታሮች እና ታክን በሚጎርሳቸው ቀለሃዎች ላይ ተደርጎ ጥይት የማይበሳቸውን ተሽከርካሪዎች የመበጣጠስ ኃይል እንዲኖረው ይሆናል።

የተባበሩት መንግሥታት አንድ ኮሚቴ ለተሟጠጠ ዩራኒየም መጋለጥ ይህ ነው የሚባል መርዛማ ኬሚካል አይረጭም ቢልም ሌላኛው የመንግሥታቱ ክንፍ የሆነው ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ይህን ጠይት የሚገጣጥሙ ሰዎች ለራድየሽን የመጋለጥ ዕድል አላቸው ይላል።

ባለፈው መጋቢት አንድ የፔንታገን ኃላፊ አሜሪካ ከዚህ በኋላ የተሟጠጠ ዩራኒየም ያለበት መሣሪያ ወደ ዩክሬን አትልክም ብለው ነበር።

አሜሪካ በተጨማሪ ፀረ-መሣሪያ እና ታክቲካዊ የአየር አሰሳ መሣሪያዎችን አልፎም ለሂማርስ ሚሳዔል የሚሆኑ ተጨማሪ የጦር መሣሪያዎችን ልታቀርብ ቃል ገብታለች።

በዋሺንግተን የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ እርምጃውን “የኢ-ሰብዓዊነት ጠቋሚ” በማለት “አሜሪካ የዩክሬን ወታደርን ውድቀት መቀበል ስለተሳናት መልሶ ማጥቃት የተባለውን እርምጃ እየደገፈች ነው” ሲል ወቅሷል።