በእንግሊዝ አንድ ግለሰብ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ላይ ባደረሰው የመኪና አደጋ በርካቶች ተጎዱ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው ሊቨርፑል ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለፁ ሳለ አንድ ግለሰብ በመኪና ባደረሰው አደጋ በርካቶች መጎዳታቸው ተዘገበ።
የመርሲሳይድ ፖሊስ እንዳለው ዎተር ስትሪት በተባለው መንገድ ላይ በርካታ ደጋፊዎች ደስታቸውን እየገለፁ እየተጓዙ ሳለ ነው አደጋው የደረሰው።
በስፍራው አቆጣጠር አመሻሹን 12፡00 አካባቢ በደረሰው አደጋው በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ተጎድተዋል።
ሁለት ሰዎች ከፍተኛ አደጋ ሲደርስባቸው 27 የሚሆኑ ደግሞ ሕክምና እያገኙ እንደሆነ ፖሊስ አስታውቋል።
ሊቨርፑል አካባቢ የሚኖር የ53 ዓመት ብሪታኒያዊ አደጋውን በማድረስ ተጠርጥሮ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።
አንድ የዓይን እማኝ ለቢቢሲ እንደተናገረው እሱና ቤተሰቡ ከመኪና አደጋው የተረፉት ለጥቂት ነው።
ግለሰቡ የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ መኪናውን እየነዳ ሲመጣ የታየ ሲሆን ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል አራት ሕፃናት እንደሚገኙበት ተዘግቧል።
ለሕይወት የሚያሰጋ ጉዳት ከደረሰባቸው ሁለት ሰዎች መካከል አንደኛው ሕፃን መሆኑን የኖርዝ ዌስት አምቡላንስ አገልግሎት አስታውቋል።
ባለሥልጣናት ክስተቱ "እንደ ሽብር ጥቃት አይቆጠርም" ብለዋል።
ሰኞ ከሰዓት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሊቨርፑል ደጋፊዎች ቡድናቸው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን አስመልክቶ ደስታቸውን ለመግለፅ ነው ወደ ጎዳና የወጡት።
ሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ በአደጋው ለተጎዱ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በሊቨርፑል ጎዳና የደረሰውን ክስተት "በጣም አሰቃቂ" ብለው የአደጋ ጊዙ ሠራተኞች ላሳዩት ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
አንድ የዓይን እማኛ እንደገለፀው ተጠርጣሪው አደጋውን ያደረሰው የሊቨርፑል ተጫዋቾችን ይዞ የነበረው አውቶብስ ካለፈ ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ነው።
ፖሊስ ተጠርጣሪው አደጋውን ለምን እንዳደረሰው እስካሁን ግልፅ አይደለም ብሏል።
የመርሲሳይድ የእሳት አደጋ ኃላፊ ኒክ ሲርል እንደለገፁት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከስፍራው ሲደርሱ ሶስት አዋቂዎች እና አንድ ሕፃን ከመኪናው ሥር ነበር።
የ48 ዓመቱ ሀሪ ራሺድ ከሚስቱና ከሁለት ታዳጊ ሴት ልጆቹ ጋር በስፍራው ተገኝቶ የነበረ ሲሆን አደጋውን አድርሷል የተባለው ግለሰብ "ሰዎችን እየገጨ ያለፈው በጎናችን ነው" ሲል የተፈጠረውን ይናገራል።
"መጀመሪያ የሰማነው 'ድው፣ ድው' የሚል ድምፅ ነው። አንዳንድ ግለሰቦች መንገድ ላይ ወድቀዋል። ራሳቸውንም የሳቱ ነበሩ። እጅግ አሳዛኝ ነው። በጣም አሳዛኝ።"















