ሜላኒያ ትራምፕ ከባለቤታቸው በተቃራኒ ፅንስ ማቋረጥን እንደሚደግፉ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሜላኒያ ትራምፕ የፅንስ ማቋረጥ መብትን በመደገፍ ከትዳር አጋሮቻቸው በተቃራኒ ከቆሙ የቀድሞ የሪፐብሊካን ቀዳማዊት እመቤቶች መካከል አንዷ ሆኑ።
ሜላኒያ በቅርቡ ለገበያ የሚቀርበው መጽሐፋቸውን በሚያስተዋውቁበት አጭር ቪዲዮ ላይ የሴቶችን “ግላዊ ነፃነት” እንደሚደግፉ ገልጸዋል። “ሁሉም ሴቶች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ያላቸው መብት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
አስተያየቱን የሰጡት በቅርቡ ሊለቀቅ በተዘጋጀው መጽሐፋቸው ግለሰባዊ ምርጫን እንደሚደግፉ የሚገልጽ ጽሁፍ በጋዜጣ ከታተመ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ሜላኒያ በጉዳዩ ላይ የያዙት አቋም ከባለቤታቸው ጋር የሚቃረን ይመስላል። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ህገ መንግስታዊ የፅንስ ማቋረጥ መብትን ሽረዋል።
በዚህም ሕጋዊ ፅንስ ማቋረጥ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ከሚሉ እና ለበርካታ አስርት ዓመታት የዘለቀውን የሪፐብሊካን ቀዳማዊ እመቤቶች አቋም አስቀጥለዋል።
እአአ በ1975 ቀዳማዊት እመቤት ቤቲ ፎርድ ዋይት ሃውስ በነበሩበት ወቅት ነው የፅንስ ማቋረጥ ሕግን “ታላቅ፣ ታላቅ ውሳኔ” ሲሉ የጠሩት።
ናንሲ ሬጋን በበኩላቸው ባለቤታቸው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ከስልጣን እስኪለቁ ድረስ ጠብቀው "በሴት ምርጫ አምናለሁ" ሲሉ በይፋ ተናግረዋል። በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም ቀደም ሲልም ዋይት ሃውስ ውስጥ በደንብ ይታወቃል ተብሏል።
የፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤች ደብሊው ቡሽ ባለቤት ባርባራ ቡሽ እና የፕሬዚዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ ባለቤት የሆኑት ላውራ ቡሽም በተመሳሳይ መንገድ ባሎቻቸው ከዋይት ሃውስ ከወጡ በኋላ በጉዳዩ ላይ ያላቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
ላውራ ቡሽ መጽሐፋቸውን ለማስተዋወቅ በሚል እአአ በ2010 በተደረገ ቃለ ምልልስ “ለጤና እና ለሰዎች ጠቃሚ ነው ብዬ ስለማስብ ሕጋዊ ሆኖ መቆየቱ አስፈላጊ ይመስለኛል” ብለዋል።
የሜላኒያ አካሄድ ግን ከዚህ የተለየ ነው።
ሜላኒያ ሐሙስ ዕለት በኤክስ አካውንታቸው ላይ በተለጠፈ ባለጥቁር እና ነጭ ቀለም ቪዲዮ ላይ “ሁሉም ሴቶች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ ስለያዙት የግለሰብ ነፃነት መብት ለመደራደር ምንም ቦታ የለም” ብለዋል ።
"ለመሆኑ ሰውነቴ፣ ምርጫዬ ምን ማለት ይሆን?" ብለዋል ሜላኒያ።
ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ መስከረም 26 ለገበያ ሊቀርብ ከተዘጋጀው እና ሜላኒያ ከተሰኘው አዲሱ መጽሐፋቸው የተለያዩ ሃሳቦችን ቀነጫጭቦ ካሳተመ ከአንድ ቀን በኋላ ነው ቪዲዮው የተለቀቀው።
“ሴቶች ከማንኛውም ጣልቃ ገብነት ወይም ከመንግስት ጫና ነፃ ሆነው፣ በራሳቸው እምነት ላይ በመመስረት ልጅ የመውለድ ምርጫቸውን የመወሰን መብት እንዲኖራቸው ዋስትና መስጠት አስፈላጊ ነው” በማለት መጻፋቸውን ዘ ጋርዲያን አስነብቧል።
“ከሴቷ በቀር ሌላ ሰው በሰውነቷ ላይ ስለምታደርገው ነገር የመወሰን ሥልጣን ለምን ይኖረዋል? አንዲት ሴት በራሷ ህይወት ላይ ያላት የግለሰብ ነፃነት፣ ከፈለገች እርግዝናዋን የማቋረጥ ሥልጣን ይሰጣታል” ሲሉ አስፍረዋል።
"አንዲት ሴት ያልተፈለገ እርግዝናን ለማቋረጥ የመወሰን መብቷን መገደብ በሰውነቷ ላይ ያላትን መብት ከመከልከል ጋር ተመሳሳይ ነው።
ይህን እምነት በህይወቴ በሙሉ ይዤው ኖሬያለሁ።"
ፈርስት ዉሜን የተሰኘው መጽሃፍ ደራሲ እና ጋዜጠኛዋ ኬት አንደርሰን ብሮወር በአስተያየቶቹ በጣም እንደተደናገጠች ተናግራለች።
"በጣም ደንግጬ ስለነበር እውነት መሆኑን ማረጋገጥ ፈለግኩኝ። ከባለቤቷ ኋላ ተሰልፋ ነበር። ባለቤቷ እሷ ከምትፈልገው ነገር ተለይቶ ሲጓዝ እነዚህን ሁሉ ዓመታት እንዴት አሳለፈች?" ብላለች።
ባለቤታቸው በድጋሚ ለመመረጥ በንቃት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በፅንስ ማቋረጥ ላይ ያላቸውን አቋም ያሳወቁ ብቸኛዋ ቀዳማዊት እመቤት ናቸው።
ሜላንያ አስተያየት የሰጡበት ጊዜ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ሊጠቁም እንደሚችልም ብሮወር ተናግራለች።
"ይህ ከምርጫው በፊት መውጣቱ ሆን ተብሎ የተደረገ አይደለም። ይልቁንም በፅንስ ማቋረጥ ሕግ መሰረዝ የተበሳጩ ግዛቶችን መራጮች ለመያዝ ነው። ምናልባት እሱ (ትራምፕ) በፅንስ ማቋረጥ ላይ እንደሚለሳለስ ምልክት አድርገው ይቆጥሩት ይሆናል" ብላለች።
የሪፐብሊካን ፓርቲ ስትራቴጂስት የሆኑት ሪና ሻህ ግን ከዚህ የተለየ አመለካከት አቅርበዋል።
"በዚህ ጊዜ ምንም ነገር አይቀይርም። ይህንንም ታውቃለች። በአንዳንድ ቦታዎች ቅድመ ምርጫዎች ተወስነዋል ስለዚህ በጣም ዘግይቷል" ሲሉ አክለዋል።
በሚቀጥለው ወር የሚካሄደው የአሜሪካን ምርጫ ፅንስ ማቋረጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው።












