አሜሪካ የትራምፕን አማካሪ ለመግደል አሲሯል የተባለውን ኢራናዊ ለያዘ 20 ሚሊዮን ዶላር እሰጣለሁ አለች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የነበሩት ጆን ቦልተንን ለመግደል አሲሯል የተባለውን ኢራናዊ ለያዘ አሊያም ያለበትን ለጠቆመ 20 ሚሊዮን ወሮታ እንደምትከፍል አስታወቀች።

የኢራን ኢስላማዊ አብዮት ዘብ አባል የሆነው ሻህራም ፑርሳፊ አሜሪካ ውስጥ ወንጀለኞችን አፈላልጎ በ300 ሺህ ዶላር በመቅጠር የኢራን ቀንደኛ ተቺ የሆኑት ቦልተንን ለማስገደል አሲሯል ተብሎ ተጠርጥሯል።

በያዝነው ሳምንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን መንግሥት የግድያ ሙከራ ሊደረግባቸው እንደሚችል የደኅንነት ሰዎች እንዳስጠነቀቋቸው ተናግረው ነበር።

ኢራን ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ወቀሳ ቀርቦባት የትራምፕን አማካሪዎች የማስገደልም ሆነ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ሐሳብ እንደሌላት ገልፃለች።

የአሜሪካ ባለሥልጣናት እንደሚሉት በአውሮፓውያኑ ከጥቅምት 2021 እስከ ሚያዚያ 2022 ባለው ጊዜ ነው ኢራናዊው ግለሰብ ጆን ቦልተንን ዋሺንግተን ዲሲ አሊያም ሜሪላንድ ውስጥ ለማስገደል ጥረት ሲያደርግ የነበረው።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደገለፀው ግድያውን እንዲፈፅሙ ከተመለመሉ ሰዎች መካከል አንዱ በድብቅ ለአሜሪካ መርማሪዎች የሚሠራ ግለሰብ ነው።

ፑርሳፊ ለዚህ ግለሰብ ነገረው እንደተባለው ከሆነ የጆን ቦልተንን ግድያ ካጠናቀቀ በኋላ “ሁለተኛ ግድያ ተዘጋጅቶልሀል” ብሎታል።

አሜሪካ የኢራኑን ጀኔራል ቃሲም ሱሌይማኒን መግደሏን ለመበቀል ነው ኢራናዊው የአብዮቱ ዘብ አባል የትራምፕን አማካሪ ለመግደል ያሴረው ተብሏል።

ጀኔራል ቃሲም ሱሌይማኒ፤ ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ ነው የተገደሉት። ትራምፕ ግድያው እንዲፈፀም እንዳዘዙ ይነገራል።

የአሜሪካ ፍትሕ ሚኒስቴር ፑርሳፊን የግድያ ወንጀል ለመፈፀም በማሴር ከሶታል። ግለሰቡ አድራሻው አይታወቅም፤ አሜሪካ ውስጥ ነው ያለው የሚል ግምትም የለም።

ከአሜሪካው ኤንቢሲ ኒውስ ጋር ቃለ-መጠይቅ ያደረጉት የኢራኑ ምክትል ፕሬዝደንት ሞሐመድ ጃቫድ ዛሪፍ መንግሥታቸው ውጭ ያሉ ተቺዎችን ለማስገደል ያሴራሉ መባሉን አስተባብለዋል።

“እኛ ሰው አንገድልም። እንደውም እውነታው ወዲህ ነው። እነሱ በጣም የተከበረ የኢራን ጀኔራል ነው የገደሉት” ብለዋል።

የቀድሞው የትራምፕ አማካሪ ቦልተን ደግሞ ሐሙስ ዕለት ኤንቢሲ ጣቢያ ላይ ቀርበው አሜሪካ ከኢራን የሚመነጩ ስጋቶችን ለመቀነስ “ነቅታ መጠበቅ አለባት” ሲሉ ተደምጠዋል።

በሳምንቱ መባቻ የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ሰዎች ከአሜሪካ ደኅንነት ባለሥልጣናት ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል ማለታቸው ይታወሳል። ማስጠንቀቂያው ኢራን ትራምፕን ለመግደል አሲራለች የሚል ነው።

የብሔራዊ ደኅንነት ዳይሬክተሩ ቢሮ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ቢቆጠብም የትራምፕ ሰዎች ያሉት ነገር እውነት መሆኑን አረጋግጧል።

ትራምፕ በበኩላቸው በኤክስ ማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው “ኢራን ሕይወቴ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደቅናለች” ሲሉ ፅፈዋል።

“ኢራን ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሙከራ አድርጋለች፤ ግን አልተሰካላትም። ድጋሚ መሞከራቸው አይቀርም” ብለዋል።

በቅርቡ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ላይ በተቃጡ ሁለት የግድያ ሙከራዎች ውስጥ የኢራን እጅ አለበት የሚል ጥርጣሬ ከአሜሪካ የደኅንነት ሰዎች ዘንድ አልተሰማም።