ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቤንዜማ ከ14 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከሪያል ማድሪድ ጋር ሊለያይ ነው
የ5 ግዜ የቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊው ካሪም ቤንዜማ ከ14 ዓመታት የማድሪድ ቆይታ በኋላ ከክለቡ ጋር ሊለያይ ነው።
የ35 ዓመቱ ቤንዜማ ከማድሪድ ጋር 5 የቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫዎችን እንዲሁም 4 የላ ሊጋ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።
ክለቡ እና ተጫዋቹ መለያየታቸውን ማድሪድ ባወጣው መግለጫ ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ በዚሁ መግለጫው ቤንዜማ የመልካም ሥነ-ምግባር እና ፕሮፌሽናል ትጋቱ የክለቡን እሴት የሚወክል ተጫዋች ነው ብሎታል።
ፈረንሳያዊው የፊት መስመር ተጫዋች ከሪያል ማድሪድ ጋር 25 ትልቅ ሰፍራ የሚሰጣቸውን ክብሮች የተቀዳጀ ሲሆን ይህም በክለቡ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።
በባለፈው የውድድር ዓመት ለክለቡ ማድሪድ በቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታዎች 15 ጎሎችን ማስቆጠር የስፔኑ ኃያል ክለብ ዋንጫ እንዲያሳ ምክንያት የሆነው ቤንዜማ የወቅቱ የባሎንዶር አሸናፊ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ አምስት የክለቦች የዓለም ዋንጫዎች እንዲሁም ሦስት የኮባ ዴላ ሬይ ክብርን መጎናጸፍ የቻለ ተጫዋች ነው ቤንዜማ።
ቤንዜማ ለማድሪድ 647 ግዜ ተሰልፎ ተጫውቶ 353 ጎሎችን ማስቆጠረ የቻለ ሲሆን፤ ከቤንዜማ በላይ ለማድሪድ ከፍተኛ ጎል ያስቆጠረው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ብቻ ነው።
ቤንዜማ የ2022/23 የውድድር ዓመት መጨረሻ በሆነው በላ ሊጋ ግጥሚያ ከአትሌቲክ ቢልባኦ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ለመጨረሻ ግዜ በማድሪድ መለያ የሚታይበት ይሆናል ተብሏል።
ክለቡ ቤንዜማ በድንቅ የእግር ኳስ ችሎታው ከክለቡ የምንግዜም ባለ ታሪከኞች መካከል አንዱ ሆኗል ብሏል በመግለጫው።
ቤንዜማ ማድሪድን ከተሰናበት በኋላ በቀጣይ ወደሚጓዝበት ክለብ በይፋ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም ባሳለፍነው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች ካሪም ቤንዜማ ወደ ሳዑዲ ሊያቀና ይችላል ሲሉ ነበር።
ይህን ዜና ተከትሎ የማድሪዱ አሠልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ፈንሳዊው አጥቂ ቤንዜማ በክለባቸው እንደሚቆይ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።