ሜሲ፣ ራሞስ፣ ሃዛርድ፣ ኢብራ. . . በክረምቱ መስኮት በነፃ ለመዘዋወር ክለብ እየጠበቁ ያሉ ከዋክብት

ታትሟል

ኤደን ሃዛርድ በፈረንጆቹ ሰኔ 30 ከሪያል ማድሪድ ጋር በስምምነት ይለያያል።

ሃዛርድ በ2019 በ89 ሚሊዮን ፓውንድ ማድሪድን ቢቀላቀልም በዚህ የውድድር ዘመን ያደረጋቸውን 6 ጨዋታዎችን ጨምሮ 54 ጊዜ ብቻ ነው በላሊ ጋ የተሰለፈው።

የ32 ዓመቱ ቤልጂየማዊ የፈረመው ውል እስከ ሰኔ 2024 የሚያቆየው ቢሆንም ማድሪድ ከተጫዋቹ መሰናባበትን መርጧል።

ማድሪድ በኦፊሴላዊ መግለጫው ለቀድሞው የቼልሲ ፊት መስመር ተጫዋች ያለውን “አድናቆት” ገልጦ “የተሳካ ጊዜ እንዲገጥመው እንመኛለን” ብሏል።

በስፔና መዲና በጉዳት የታጀቡ ዓመታትን ያሳለፈው ሃዛርድ ቻምፒዮንስ ሊግ፣ የዓለም ክለቦች ዋንጫ፣ 2 ላሊ ጋ እና ሌሎች ዋንጫዎችን ማንሳት ችሏል።

ቼልሲ እያለ በ352 ጨዋታዎች 110 ጎሎችን በስሙ ያስመዘገበው ሃዛርድ በማድሪድ ቤት በጠቅላላው 76 ጨዋዋታዎችን ያደረገው ሃዛርድ 7 ጎሎችን አስቆጥሯል።

በሌላ ዜና የማድሪዱ አሠልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ ፈንሳዊው አጥቂ ቤንዜማ በክለባቸው እንደሚቆይ ተስፋ እንዳላቸው ቢናገሩም ቤንዜማ ከክለቡ መለያየቱ ይፋ ሆኗል።።

ባሳለፍነው ሳምንት የወጡ ዘገባዎች ካሪም ቤንዜማ ወደ ሳዑዲ ሊያቀና ይችላል ሲሉ ነበር።

ወደ ፈረንሳይ ስናቀና ሊዮኔል ሜሲና ሰርጊዮ ራሞስ፤ ፒኤስጂ በተሸነፈበት ግጥሚያ የመጨረሻ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

ተከላካዩ ራሞስ በጭንቅላት ያስቆጠራት ጎል ፒኤስጂን ቀዳሚ አድርጋለች። ምባፔ የፍፁም ቅጣት ምት አክሎ ፒኤስጂ ጨዋታውን 2-0 ሲመራ ቆይቶ ነው የኋላ ኋላ የተረታው።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ስሙ ሲጠራ በአንዳንድ የፈረንሳዩ ክለብ ደጋፊዎች የተቃውሞ ድምፅ የተሰማበት ሜሲ በርካታ አጋጣሚዎችን ሳይጠቀም ቀርቷል።

ሊዮኔል ሜሲ እና ሰርጂዮ ራሞስ ከፒኤስጂ ጋር ያላቸው ውል ተጠናቋል።

ሜሲ ወደ ሳዑዲ አራቢያው አል ሂላል አሊያም ወደ አሜሪካው ኢንተር ማያሚ ሊያቀና እንደሚችል ተገልጧል።

የኤሲ ሚላኑ ዝላታን ኢብራሂሞቪች እሑድ ከሚደረገው የመጨረሻው የሴሪ አ ጨዋታ በኋላ ክለቡን ይሰናበታል።

የጣሊያኑ ክለብ እንደገለጠው ለ41 ዓመቱ ስዊዲናዊ የሽኝት ፕሮግራም ይደረግለታል።

በጉዳት ምክንያት በተገባደደው የውድድር ዘመን ብዙ ጨዋታዎች ያመለጡት ኢብራ ከኤሲ ሚላን ጋር ያለው ተጠናቋል።

ለማልሞ፣ አያክስ፣ ኢንተር ሚላን፣ ባርሴሎና፣ ፒኤስጂ፣ ኤልኤ ጋላክሲና ማንቸስተር ዩናይትድ የተጫወተው ኢብራ ቀጥሎ ወደየት እንደሚያቀና አልታወቀም።