መርሴዲስ “ፍሬናቸው” ችግር አለበት በሚል 1 ሚሊዮን መኪናዎችን ለጥገና ጠራ

ሜርሴዲስ ቤንዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የጀርመኑ መኪና አምራች ኩባንያ መርሴዲስ-ቤንዝ 1 ሚሊዮን ገደማ አሮጌ መኪናዎችን ለጥገና ጠርቷል።

ኩባንያው እኚህ መኪናዎች ፍሬናቸው ችግር አለባቸውና ጠግኜ ልመልስላችሁ ብሏል።

ሜርሴዲስ ይህን ያለው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ነው።

ኩባንያው መኪኖቹ ከፍተኛ በሆነ ዝገት ምክንያት የፍሬን ሰርዓታቸው ተገቢውን ሥራ ላይሰራ ይችላል ብሏል።

ጀርመን ያሉ 70 ሺህ መኪናዎችን ጨምሮ ከ993 ሺህ በላይ መኪናዎች መጠገን አለባቸው።

መርሴዲስ ባለፈው ዓመትም እንዲሁ ገዘፍ ያለ ቁጥር ያለው መኪና በደኅንነት ምክንያት ለጥገና ጠርቶ ነበር።

ኩባንያው ለጥገና የጠራቸው መኪናዎች በፈረንጆቹ ከ2004 እስከ 2014 ድረስ የተመረቱ ናቸው።

ኤምኤልና ጂኤል በመባል የሚታወቁት ቅንጡ ሞዴሎች ናቸው ጥገና ያሻቸው።

መርሴዲስ ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫው “አድቫንስድ ኮሮዥን” ተፈጥሮ ፍሬን አልሠራም ከማለቱ በፊት ነው መኪናዎቹን የጠራናቸው ተብሏል።

መግለጫው አክሎ ምናልባት ፍሬን አልሠራ ብሎ አደጋ የመፈጠሩ ዕድል ከፍ እንዳይል ነው ይህን ማድረግ ያስፈገን ብሏል።

መኪናዎቹ ከተጠሩ በኋላ ይህ ችግር ካለባቸው ጥገና ይደረግላቸዋል። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አዳዲስ ክፍሎች ሊገጠምላቸው ይችላል።

ሜርሴዲስ በተመሳሳይ ባለፈው የካቲት 1 ሚሊዮን መኪናዎች ተጠርተው “ኢ-ኮል” የተሰኘው ቴክኖሎጂያቸው እንዲፈተሽ አድርጎ ነበር።

ይህ ቴክኖሎጂ የመኪናውን ትክክለኛ አድራሻ ለይቶ የሚልክ ነው።

አውሮፓ ውስጥ ይህን ቴክኖሎጂ ሳይጠቀሙ ከ2018 በኋላ የተሸጡ መኪናዎችን ማሽከርከር አይቻልም።