ከ11 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የተደረገበት የቀድሞው ጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ስርዓተ ቀብር ዛሬ ይከናወናል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከጥቂት ወራት በፊት በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ያለፈው የቀድሞው ጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ስርዓተ ቀብር የዓለም መሪዎችን ቀልብ በመሳብና በአወዛጋቢነቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
ከሳምንት በፊት የብሪታንያ ንግሥት ኤልዛቤጥ ሁለተኛ የቀብር ስነ ስርዓት ለመታደም የዓለም ዓቀፉ መሪዎችና ተፅእኖ ፈጣሪዎች በለንደን ተሰባስበው ነበር።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በዛሬው ዕለት ለሚከናወነው ለቀድሞው የጃፓን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ስርዓተ ቀብር በጃፓን ተገኝተዋል።
ነገር ግን ጃፓናውያን በዚህ ሸብ ረብ በበባዘበት ብሔራዊ የቀብር የቀብር ስነ ስርዓት ደስተኞች አይደሉም። ለዚህም አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓቱ ቢያንስ 11.4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ማስወጣቱ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የሚደረገው ተቃውሞ እየጨመረ መጥቷል።
የህዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ከግማሽ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ ህዝብ የቀብር ስርዓቱ በዚህ መልክ መከናወኑን ይቃወማል።
ጥግ የደረሰው ማሳያ ተቃውሞም ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በቶኪዮ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አቅራቢያ አንድ ሰው ራሱን ማቃጠሉ ነው።
እንዲሁም ሰኞ እለት ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ ተቃዋሚዎች ብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓቱ እንዲሰረዝ በመዲናይቱ ጎዳናዎች ላይ ወጥተዋል።
ነገር ግን በሌላ መልኩ ክስተቱ የጃፓን አጋር የሆኑ አገራት መሪዎችን በማሰባሰብ ቀልብ ስቧል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ባይገኙም ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ ይገኛሉ። የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ህሲየን እንዲሁ ይታደማሉ።
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ከቀድሞ የአገራቸው ሶስት መሪዎች ጋር እንዲሁ ይገኛሉ።
በንግሥቲቱ የቀብር ሥነስርዓት ላይ ያልተገኙት የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ለአቤ ክብራቸውን ለመግለጽ ቶኪዮ ተገኝተዋል።
የዓለም መሪዎች ለቀብር ስነ ስርዓታቸው በተሰባሰቡበት ሁኔታ የአገሬው ሰው በዚህ መልኩ መቃወሙ ስለ አቤ ምን ይላል።
በመጀመሪያ ደረጃ እንዲህ አይነት ብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት የተለመደ ክስተት አይደለም።
በጃፓን ብሔራዊ የቀብር ሥነ ስርዓቶች ንጉሳውያን ቤተሰቦች ሲሞቱ ብቻ የሚከወኑ ናቸው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓውያኑ 1967 ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻ ለአንድ ፖለቲከኛ ብሄራዊ የቀብር ስነ ስርዓት ተካሂዷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የሺንዞ አቤ ብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት መደረጉ እንደ ትልቅ ነገር ነው የሚታየው።
በከፊልም ከሺንዞ አቤ ሞት ጋር ይያያዛል። ሐምሌ ወር ላይ በነበረ የምርጫ ዘመቻ ላይ በጥይት ተመትተው ነው ህይወታቸው ያለፈው።
በርካታ ጃፓናውያንም በቀድሞው መሪ ሞት ድንጋጤያቸውንና ኃዘናቸውን ገልጸዋል። የህዝብ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት አቤ ተወዳጅ አልነበሩም ነገር ግን ጥቂቶች ለሃገሪቱ መረጋጋትና ደህንነት እንዳመጡ አይክዱም።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ለእሳቸው ብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት እንዲካሄድ መወሰኑ ያላቸውን ተፅእኖም ነጸብራቅ ነው።
በጃፓን ታሪክ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በጠቅላይ ሚኒስትርነት በማገልገል ታሪክ ይጠቅሳቸዋል። በተጨማሪም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአለም ላይ የጃፓንን ሚና በማጉላት ተወዳዳሪ አልተገኘላቸውም።












