ስዊትዘርላንዳውያን በሕዝበ ውሳኔ ለራሳቸው ከፍተኛ የጡረታ አበል ጭማሪ እንዲደረግ ወሰኑ

የፎቶው ባለመብት, AFP VIA GETTY IMAGES
ስዊትዘርላንዳዊያን በየወሩ የሚያገኙት የጡረታ አበል በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር በመላ አገሪቱ በተካሄደ ሕዝበ ውሳኔ ወሰኑ።
ሕዝበ ውሳኔው ለጡረታ ዕድሜ የደረሱ የአገሪቱ ዜጎች የጡረታ ገንዘብ ከፍ ይበል ወይስ አይበል የሚል ነበር።
የአገሪቱ መንግሥት ግን እየጫናችሁብኝ ያለው ዕዳ ከባድ ነው ሲል ምሬቱን ገልጧል።
ነገር ግን በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ከሰጡ ዜጎች መካከል 60 በመቶው የጡረታ አበል ከፍ እንዲል ድምፃቸውን ሰጥተዋል።
በተያያዘ ሕዝበ-ውሳኔ የጡረታ ዕድሜ ከ65 ወደ 66 ከፍ ይበል የሚለውን ሐሳብ ዜጎች ውድቅ አድርገውታል።
በስዊትዘርላንድ ከፍተኛው የጡረታ ክፍያ 2550 ዩሮ ሲሆን ስዊዞች ግን ይህ በቂ አይደለም ይላሉ።
ስዊትዘርላንድ በዓለማችን ኑሮ ውድ ከሚባልባቸው አገራት መካከል ስትሆን፣ በተለይ ደግሞ እንደ ዙሪክ እና ጄኔቫ ባሉ ከተማዎች ኑሮ አይቀመስም።
በአገሪቱ የጤና ኢንሹራንስ ሁሉም ሰው ሊኖረው ግድ ሲሆን፣ ነገር ግን በተለይ በዕድሜ የገፉ ሰዎች ይህን መክፈል አልቻልንም ሲሉ ያማርራሉ።
ልጆች ለማሳደግ በሚል ሥራ የለቀቁ ሴቶች እና ከዓመታት በፊት በስዊዝ ፋብሪካዎች፣ ሬስቶራንቶች እና ሆስፒታሎች እንዲሠሩ ተመልምለው የመጡ ስደተኞች ኑሮ ከብዷቸዋል።
አብዛኛዎቹ የአገሪቱ ዜጎች በ70ዎቹ ዕድሜ ላይ ሆነውም ቢሆንም ሥራ የሚቀጥሉ ሲሆን፣ ይህ ኑሮን ለማሸነፍ ምርጫ ከማጣት የመጣ ነው ተብሏል።
በሌላ በኩል ወጣቶች ከሥራ ብዛት ጭንቀት እና ድካም እየተጫጫናቸው ይገኛል።
አሁን ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደበትን የጡረታ አበል ጭማሪን በተመለከተ ሃሳቡን ያፈለቀው የሠራተኛ ማኅበራት ጥምረት ነው።
መጀመሪያ ይህ ሐሳብ ሲቀርብ የአገሪቱ መንግሥት፣ ፓርላማው እና ባለሀብቶች መጠኑ እጅግ በዛ ሲሉ ተቃውመውት ነበር።
ስዊትዘርላንዳውያን ብዙውን ጊዜ መንግሥት የሚያቀርብላቸውን ሐሳብ ይሰማሉ። እንዲያውም ከጥቂት ዓመታት በፊት በዓመት አንድ ተጨማሪ የእረፍት ቀን ይሰጣችሁ ተብለው እምቢ ማለታቸው መነጋገሪያ ነበር።
ቢሆንም የጡረታ አበል ይጨመር ወይ ብለው ሲጠየቁ እምቢኝ አላሉም። ዜጎች የአገሪቱን ቀጥተኛ የዲሞክራሲ ሥርዓትን ተጠቅመው በአብላጫ ድምፅ ለራሳቸው ከፍተኛ የጡረታ አበል ጨምረዋል።
ውጤቱ ለስዊዝ ጡረተኞች “ትልቅ እመርታ” ነው ተብሏል።
ይህ ማለት በሚቀጥለው ኅዳር ጡረተኞች ከዚህ ቀደም የሚያገኙትን ክፍያ እጥፍ ያገኛሉ ማለት ነው።
ስዊትዘርላንድ ከጡረተኞች ክፍያ ላይ ግብር የምትቆርጥ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ብዙዎችን ቅር የሚያሰኝ ነው።
መንግሥት በተደጋጋሚ ሕዝበ ወሳኔው አደገኛ ነው፤ የመክፈል አቅም የለኝም ቢልም ዜጎች ግን አሻፈረኝ ብለው ድምፃቸውን ተጠቅመው ጡረታ ጨምረዋል።












