ተራራ ወጭዎች ክብረ ወሰን ለመስበር በሚል በሞት አፋፍ ላይ የነበረን ፓኪስታናዊ አስጎብኚ ተራምደውት አልፈዋል ተባለ

የፓኪስታኑ ኬቱ ተራራ

የፎቶው ባለመብት, Wilhelm Steindl

ታትሟል

ክብረ ወሰን ለመስበር በሚል በሞት አፋፍ ላይ የነበረውን ፓኪስታናዊ አስጎብኚ ተራምደውት አልፈውታል የተባሉት ተራራ ወጪዎች አስተባበሉ።

ተራራ ወጭዎቹ በፓኪስታን ኬቱ የተሰኘውን የዓለማችን ሁለተኛውን ከፍተኛ ተራራ እየወጡ በነበረበት ወቅት የተጎዳውንና በኋላ ህይወቱ ያለፈውን አስጎብኚ ተረማምደው አልፈውታል ተብሏል።

ይህንንም ክስ ታዋቂዋ የኖርዌይ ተራራ ወጭ አልተቀበለችውም።

መሃመድ ሃሰን በተራራው ላይ ከወደቀ በኋላ ተራራ ወጭዎቹ ተረማምደውበት ሲያልፉ የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ የወጣ ሲሆን ግለሰቡ ከሰዓታት በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

ነገር ክርስቲን ሃሪላ የተሰኘችው ተራራ ወጭ ለቢቢሲ የተናገረችው እሷ እና የተራራ ወጭው ቡድን አባላት በአደገኛ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነው የአስጎብኝውን ሕይወት ለመታደግ የሚችሉትን ሁሉ እንዳደረጉ ነው።

“ይህ አሳዛኝ አደጋ ነው። በኬቱ ተራራ የልጆች አባት፣ ባል የሆነውን ሰው ሕይወት አጥተናል። በዚህ መንገድ መቋጨቱ በጣም የሚያሳዝን ነው” ብላለች።

ይህች ተራራ ወጭ ከ8 ሺህ ሜትር (26 ሺህ ጫማ) በላይ የሆነውን የኬቱ ተራራ በመውጣትና በፍጥነትም በማጠናቀቅም ክብረ ወሰንን ለማስመዝገብ እያቀናች ነበር።

ከሁለት ሳምንታት በፊትም በነበረው የተራራ መውጣትም ላይ መሃመድ ሃስን በተራራው “የጠርሙስ አንገት” ተብሎ በሚጠራው ጠባብ መንገድ ላይም መውደቁ ተዘግቧል።

ከኦስትሪያ የመጡ ሁለት ተራራ ወጭዎች ፍሊፕ ፍሌሚንግ እና ዊልሄልም ስቴንድል ተራራ ወጭዎች በተጎዳው ጎብኝ ላይ ተረማምደው ሲተላለፉም የሚያሳይ ፎቶ ለጥፈዋል።

ሁለቱ ግለሰቦች በእለቱ ተራራውን ሲወጡ የነበሩ ሲሆን በአደገኛ የአየር ሁኔታ እና ውሽንፍር በተሞላበት ዝናብ ምክንያት ተራራው ጫፍ ላይ ለመድረስ የነበራቸው ዕቅድ ላይ ደርሰዋል።

ግለሰቦቹም ዊልሄልም ስቴንድል ተራራው ጫፍ ላይ ለመውጣት የሚያደርገውን ሙከራ የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ሲቀርጹ ነበር።

በካሜራቸው የዚያን እለት የሆነውን ማየት ባይችሉም በሰው አልባ አውሮፕላን (በድሮን) የተቀረጸውን በማግስቱ ማየታቸውን አስታውቀዋል።

“በሕይወት ያለ አንድ ግለሰብ በተራራው መንገድ ላይ ወድቆ አየን። እናም ተራራ ወጭዎች በላዩ ላይ እየተረማመዱ አልፈውታል። ሕይወቱን የመታደግ ሙከራም አልነበረም” ሲሉም ስቴንድል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“በጣም አስደንጋጭ ነው። ደንግጫለሁ፣ አዝኛለሁ። እየተረማመዱት ሲያልፉትም አይቼ ማልቀስ ጀመርኩ። ለመርዳትም አልሞከሩም” ብለዋል።