ስድስት ሩሲያውያን ተራራ ወጭዎች በእሳተ ገሞራ ላይ ወድቀው ሞቱ

የሩሲያ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በምስራቅ ሩሲያ በምትገኘው ምሥራቃዊ ካምቻትካ ግዛት በእሳተ ገሞራ የተፈጠረ ተራራ ለመውጣት የሞከሩ ቢያንስ 6 ተራራ ወጭዎች ህይወታቸው ማለፉን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በመጥፎ የአየር ጠባይ ምክንያት የነፍስ አድን ሠራተኞች ስድስቱን ተራራ ወጪዎች ማዳን አልቻልንም ብለዋል ።

ሁለቱ ሰዎች ከባህር ወለል በላይ በ3 ሺህ 300 ሜትር ከፍታ ላይ የነበሩ ሲሆን ሌሎቹ አራት ደግሞ በ4 ሺህ ሜትር ከፍታ ላይ እንደደነበሩ ይታመናል።

ሁሉም ግለሰቦች የሩሲያ ዜጎች ናቸው።

 ሁለት አስጎብኚዎችን ጨምሮ አስራ ሁለት ግለሰቦችን ያካተተው ቡድን ማክሰኞ ዕለት ነበር ወደ 4 ሺህ 754 ሜትር ከፍታ ተራራ ለመውጣት ጉዞ የጀመረው።

ከአራት ቀናት በኋላ ከ4,000 ሜትር ከፍታ የወደቁት አራት ተራራ ወጭዎች ወዲያውኑ ህይወታቸው አልፏል ተብሎ ይታመናል። ሌሎች ሁለት ተራራ ወጭዎችም ብዙም ሳይቆዩ ሞተዋል።

ከአስጎብኚዎቹ አንዱ እግሩን እንደሰበረ የተነገረ ሲሆን የቀሩት ሰዎች ሁኔታ ግን በውል አልታወቀም።

ክልዩቼቭስካያ ሶፕካ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የካምቻትካ የተፈጥሮ እሳተ ገሞራዎች አካል ነው።

እሳተ ገሞራው በአንዳንድ የአገሬው ተወላጆች ዘንድ እንደ ቅዱስ ስፍራ ይቆጠራል።