በሂማሊያ ተራራ ላይ የጠፉት 8 ተራራ ወጪዎች እየተፈለጉ ነው

ናንዳ ዴቪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቡድኑ አባላት የጠፉት ናንዳ ዴቪ ተሰኘውን የሂማሊያ ተራራ በመውጣት ላይ ሳሉ ነበር
ታትሟል

ከሰሞኑ የተራራ ወጪዎች ሞትን የተመለከቱ ዜናዎች ተበራክተዋል፤ ባለፈው ኤቨረስት ተራራን በመውጣት ላይ የነበሩና ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር በርካቶች ሕይወታቸው አልፏል።

አሁን ደግሞ በሕንድ ሂማሊያ ተራራን በመውጣት ላይ የነበረ ስምንት አባላት ያሉት አንድ ቡድን የት እንደደረሰ አልታወቀም።

አራት እንግሊዛውያንን ጨምሮ ሌሎች የቡድኑ አባላት በሂማሊያ ተራራዎች ከባህር ጠለል በላይ 7816 ሜትር ከፍታ ያለውን ናንዳ ዴቪ መውጣት የጀመሩት ከ15 ቀናት ገደማ በፊት ነበር።

ቡድኑ አራት እንግሊዛዊያን፣ ሁለት አሜሪካዊያን፣ አውስትራሊያዊና ሕንዳዊ ይገኙበታል።

በተያዘው እቅድ መሠረት ተራራ ወጪዎቹ በተራራው ግርጌ ወደሚገኘው ካምፕ ሳይመለሱ ሲቀሩ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ ቡድን ለፍለጋ ወደ ሥፍራው አቅንቷል።

ይሁን እንጂ የበረዶ መንሸራተትና ከፍተኛ ዝናብ በተራራው ላይ የሚደረገውን ፍለጋ ሊያስተጓጉለው እንደሚችል የአካባቢው ባለሥልጣናት አስጠንቅቀዋል።

"ተራራ ወጪዎቹ ለመፈለግ የሚያስፈልገንን አሟልተናል፤ ይሁን አንጂ በአካባቢው ያለው መጥፎ የአየር ጠባይ ፍለጋውን አስቸጋሪ አድርጎታል" ሲሉ የፒቶራጋር ግዛት ባለሥልጣን ቪጃይ ኩማር ለኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

የሕንድ አየር ኃይል ሄሊኮፕተርም ዛሬ ጠዋት ለፍለጋ እንደሚሰማራ ተገልጿል።

ቡድኑ እየተመራ የነበረው ልምድ ባለው እንግሊዛዊ ተራራ ወጪ ማርቲን ሞራን ሲሆን፤ ማርቲን ተቀማጭነቱን ስኮትላንድ ያደረገ በሕንድ ሂማሊያ ተራራ ወጪዎችን በተመለከተ በርካታ ሥራ የሚያከናውን ድርጅት አለው።

ተራራውን መውጣት ከመጀመራቸው ከአንድ ቀን በፊት ማርቲን በፌስቡክ ገፁ ላይ የለጠፈው ፎቶ ቡድኑ ተራራ ለመውጣት ጉዞውን ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ያሳያል።

በፈረንጆቹ ሜይ 22 ከለጠፈው በኋላ በሁለተኛው ካምፕ (4870 ሜትር ከፍታ ላይ) ቡድኑ የተራራው ጫፍ ላይ ሳይደርሱ ጉዟቸውን እንደማያጠናቅቁ አስተያየቱን አስፍሯል።

ይሁን እንጂ ቡድኑ ለመመለስ ያሰበበትን ቀን አስመልክቶ ያሉት የተለያዩ ሪፖርቶች ናቸው። በናንዳ ዴቪ ተራራ ግርጌ ካለው ካምፕ መመለስ የነበረባቸው ከሁለት ቀናት በፊት እንደነበርና በአቅራቢያው ወዳለው መንደር መግባት የነበረባቸው ትናንት እንደሆነ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ "የእንግሊዝ ዜጎች በሕንድ ሂማሊያ ተራራ መጥፋታቸውን ተከትሎ ከሕንድ ባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገርን ነው፤ እርዳታችንን ለሚሹ እንግሊዛውያን የሚቻለንን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን" ሲሉ ተናግረዋል።