በፕሪጎዢን ጄት የአደጋ ሥፍራ አስክሬኖችና የበረራ ድምጽ መቅጃዎች መገኘታቸውን ሩሲያ አስታወቀች

የፕሪጎዢን አውሮፕላን ስባሪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

የቫግነሩ አለቃ ዮቭጌኒ ፕሪጎዢን እንደሞቱበት በተነገረው የጄት አደጋ ሥፍራ 10 አስክሬኖችና የበረራ ድምጽ መቅጃዎች መገኘታቸውን ሩሲያ አስታወቀች።

የዘረ መል ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነም መርማሪዎች ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ በሞስኮ አቅራቢያ የተከሰከሰው ረቡዕ ዕለት ሲሆን በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረ ቦምብ አሊያም የሚሳይል ጥቃት ለአደጋው መንስዔ ሳይሆን እንደማይቀር እየተነገረ ነው።

የሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን በበኩላቸው ክሬሚሊን ፕሪጎዢን እንዲገደል ትዕዛዝ ሰጥታለች መባሉን “ሐሰት” ብለዋል።

የፑቲን ታማኝ የነበረው ፕሪጎዢን ሰኔ ወር ላይ ያካሄደው ወታደራዊ አመጽ ፑቲን እጅግ አስቆጥቶ የነበረ ሲሆን ድርጊቱንም “ክህደት” ብለውታል።

ለ24 ሰዓታት ብቻ የቆየው አመጽ ከከሸፈ በኋላ በተደረገ ንግግርም የቫግነር ተዋጊዎች የሩሲያን መደበኛ ጦር እንዲቀላቀሉ ወይም የሞስኮ አጋር ወደሆነችው ቤላሩስ እንዲሄዱ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር።

ይህ ስምምነት ቢደረግም ግን በርካቶች ከአመጹ በኋላ የሩሲያው ፕሬዚደንት የቫግነሩን መሪ ይቅር አይለውም በማለት የ62 ዓመቱ ፕሪጎዢን በሞት ጥላ ሥር እንደነበር ሲገልጹ ቆይተዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከሩሲያ መዲና ሰሜን ምዕራብ በሚገኘው ትቨር ክልል ረቡዕ ዕለት ባጋጠመው እና 10 ሰዎች በሞቱበት “አሳዛኝ” ክስተት ዙሪያ በርካታ መላምቶች እንዳሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ፕሪጎዢንና ቀኝ እጁ ዲሚትሪ ኡትኪን እንዲሁም አምስት ሌሎች መንገደኞችን እና ሦስት የበረራ ቡድን አባላት በኢምብሬር ሌጋሲ 600 ጄት ላይ ተሳፍረው እንደነበር የመንገደኞችን ዝርዝር የያዘው ሰነድ አመልክቷል።

ፔስኮቭ በመግለጫቸው “በምዕራቡ ዓለም፣ ከተለያየ አቅጣጫ መላምት ይሰጣል፤ ግን ሩሲያ ፕሪጎዢን እንዲገደል አዛለች መባሉ ሐሰት ነው” ብለዋል።

“ አሁን ላይ ብዙ መረጃዎች የሉንም።የሚወጡ መረጃዎችም አሁን እየተካሄደ ባለው ምርመራ መረጋገጥ አለባቸው” ሲሉም አክለዋል።

ሆኖም ፔስኮቭ ፕሪጎዢን በጄቱ ውስጥ መሳፈሩን ከሚያሳየው የስም ዝርዝር ባሻገር በተከሰከሰው አውሮፕላን ውስጥ ስለመኖሩ ክሬምሊን ማረጋገጫ እንዳላት ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም።

ፕሪጎዢን መሞቱ ከተነገረ በኋላም የቅጥረኛው ተዋጊ ቡድን ቫግነር የወደፊት እጣ ፈንታ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

አርብ ዕለት የቤላሩሱ መሪ አሌክሳንደር ሉካሽንኮ 10 ሺህ የሚሆኑ የቫግነር ተዋጊዎች በአገሪቷ ውስጥ ሆነው ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ሆኖም በርካታ ባለሙያዎች ሉካሽንኮ ይህን ያሉት ከክሬምሊን ትዕዛዝ ተቀብለው ነው ብለው ያምናሉ።

ፕሬዚደንት ፑቲን አደጋው ከደረሰ በኋላ ለተጎጂ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ሐዘን የገለጹት ለ24 ሰዓታት ምንም አስተያየት ሳይሰጡ ከቆዩ በኋላ ሲሆን፣ይህም ጥያቄን አጭሯል።

ሐዘናቸውን በገለጹበት መልዕክትም “በሕይወቱ ከባድ ስህተቶችን የሰራ ተሰጥኦ ያለው ሰው ነበር” ሲሉም ነበር ፕሪጎዢንን የገለጹት።

እስካሁን ፕሪጎዢንን አሳፍሮ ነበር የተባለው አውሮፕላን የተከሰከሰበት መንስኤ በትክክል ያልታወቀ ሲሆን፣ ከተከሰከሰበት ቅጽበት አንስቶ ብዙ መላምቶች እየተሰነዘሩ ነው።

ፔንታገን የቫግነሩ አለቃ ሳይገደል እንዳልቀረ የገለጸ ሲሆን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ደግሞ የአደጋው መንስኤ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበረ ቦምብ ሊሆን እንደሚችል ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ባይደንም አሜሪካ አውሮፕላኑ የተከሰከሰበትን ምክንያት ለማወቅ እየሞከረች ነው ብለዋል።