በኦርቶዶክስ ገዳም ውስጥ ከተደረገ የተኩስ ልውውጥ በኋላ ኮሶቮና ሰርቢያ ተፋጠጡ

የፎቶው ባለመብት, REUTERS
የሰርቢያ የዘር ሀረግ ያላቸው ታጣቂዎች እና የሰሜናዊ ኮሶቮ ፖሊስ ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ ኮሶቮ እና ሰርቢያ እርስ በርሳቸው እየተካሰሱ ይገኛሉ።
ትናንት ዕሁድ በሰርቢያ ባንጃስካ በተሰኘ ግዛት በሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ገዳም ውስጥ በነበረ ከበባ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ አንድ ፖሊስና ሶስት ታጣቂዎች ተገድለዋል።
የኮሶቮው ጠቅላይ ሚኒስትር አልቢን ኩርቲ ሰርቢያ ታጣቂዎችን ትደግፋለች ሲሉ ከሰዋል።
የሰርቢያው ፕሬዝዳንት አሌክስአንደር ቩቺች በበኩላቸው የኮሶቮ ባለስልጣናት ለተከሰተው ሞት የመጨረሻውን ኃላፊነት ይወስዳሉ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የተገደሉት ሶስት ታጣቂዎች የኮሰቮ የዘር ሀረግ ያላቸው ሰርቢያውያን ናቸው ብለዋል።
የትናንትናው ግጭት በሁለቱ ሀገራት መካከል በዓመታት ከታዩት መካረር አንዱ ሲሆን ከወራት በፊት ውጥረት ውስጥ ቆይተው ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2008 ኮሶቮ ከሰርቢያ ተነጥላ ነጻ ሀገር መሆኗን አውጃለች።
ሆኗም ሰርቢያና ቁልፍ አጋሮቿ ቻይናና ሩስያ እውቅና አልሰጧትም።
በርካታ ሰርቢያውያን የሀገራቸው ምስረታ መነሻ ኮሶቮ እንደሆነች ያምናሉ።
በኮሶቮ ከሚኖሩ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 92 በመቶዎቹ የአልቤኒያ የዘር ሀረግ ያላቸው ሲሆን 6 በመቶዎቹ ብቻ ከሰርቢያ የሚመዘዝ የዘር ሀረግ አላቸው።
እንደ ኮሶቮ ፖሊስ ገለጻ ከሆነ ታጣቂዎች በባንጃስካ አከባቢ በሰርቢያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኘው የኦርቶዶክስ ገዳም ውስጥ ከባድ መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ከገቡ በኋላ ተኩስ ተከፍቷል።
ፖሊስ ባካሄደው እና የኮሶቮ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒትር ሄላል ስቬላ “የማጽዳት ዘመቻ” ሲሉ በጠሩት ዘመቻ በተደረገ የተኩስ ልውውጥ ሶስት ታጣቂዎች ተገድለዋል።
ሚኒስትሩ “ይህንን ግዛት በቁጥጥር ስር አውለነዋል። ይህ የሆነው ከተከታታይና በርካታ ውጊያ በኋላ ነው” ብለዋል።
የአካባቢው ባለስልጣናት ስድስት ሰዎች መታሰራቸውን እና በርካታ ቁጥር ያለው መሳሪያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግረዋል።
ባለስልጣናቱ የታሰሩት ሰዎች በጥቃት ውስጥ ስላላቸው ተሳትፎ ያሉት ነገር የለም።
ታጣቂዎቹ በለሊት ገዳሙን ለቀው መውጣታቸውን የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መግለጿን ሮይተርስ ዘግቧል።
ገዳሙ ከመያዙ አስቀድሞ አንድ የኮሶቮ ፖሊስ ተገድሏል።
የኮሶቮው ጠቅላይ ሚኒስትር አልቢን ኩርቲ “ሰርቢያ ወንጀለኞችን ትደግፋለች” ሲሉ ተጠያቂ አደርገዋል።
ታጣቂዎቹን በተመለከተ ደግሞ “የሰለጠኑና የወታደር እንዲሁም የፖሊስ የኋላ ታሪክ ያላቸው” ናቸው ያለ ሲሆን በሰርቢያ በገንዘብ እና በሞራል የሚደገፉ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
የሰርቢያው ፕሬዝዳንት አሌክስአንደር ቩቺች ደግሞ የኮሶቮው ጠቅላይ ሚኒስትር ኩርቲን ለወራት “ሲተነኩሱን ነበር” ሲሉ ከሷቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, KOSOVO GOVERNMENT/HANDOUT VIA REUTERS
የኮሶቮ ፖሊስን ግድያን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ደግሞ “ፍጹም ሊወገዝ የሚገባው” ነው ካሉ በኋላ ለክስተቱ የኮሶቮው ጠቅላይ ሚኒስትር ኩርቲ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።
“ብቸኛ ምኞቱ እኛን ጎትቶ ከኔቶ ጋር ጦርነት ውስጥ መክተት ነው። ሁሉንም ቀን የሚያደርገው ብቸኛ ተግባር እሱ ነው” ሲሉም አክለዋል።
ፕሬዝዳንት ቩቺች በኔቶ የሚመራው የሰላም አስከባሪ ጣልቃ ገብቶ ቢሆን ኖሮ የጉዳቱ ሰለባዎች ቁጥር ይቀንስ ነበርም ብለዋል።
በኮሶቮ ወደ 4 ሺህ 500 የሰላም አስከባሪዎች ተሰማርተዋል።
የአውሮፓ ህብረት የውጪ ጉዳይ ፖሊስ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ክስተቱን ያወገዙት ሲሆን “አስቀያሚ ጥቃት” ሲሉም ጠርተውታል። ለጥቃቱ ኃላፊነት የሚወስዱ ሰዎች ለፍትህ ሊቀርቡ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
ባለፈው ሰኔ ወር በኮሶቮ የአካባቢ ምርጫ ተካሂዶ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኃላ በሀገሪቱ ውጥረት ነግሶ ነበር።
የሰርቢያ የዘር ሀረግ ያላቸው ሰዎች በሚበዙባቸው አከባቢዎች ነዋሪዎች ራሳቸው ከምርጫ ያገለሉ ሲሆን የኮሶቮ አልቤኒያ ፖለቲከኞች ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል።
ጆሴፍ ቦሬል ፕሬዝዳንት ኩርቲ የሰርብ የዘር ሀረግ ያላቸው ሰዎች በሚበዙበት ቦታ የበለጠ ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን የሚሰጣቸው የማዘጋጃ ቤት ማህብር እንዲመሰረቱ አላገዙም ሲሉ ወቅሰዋል።
ኔቶ ምርጫውን ተከትሎ ከተከሰተው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ተጨማሪ 700 ወታደሮቸን ወደ ኮሶቮ አሰማርቷል።
ያኔ በተፈጠረው ግጭት 30 ገደማ የሚሆኑ የኔቶ የሰላም አስከባሪዎችና ከ50 በላይ የሚሆኖ ሰርቢያዊ ተቃዋሚዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።












