ለግብፅ መንግሥት ሲሠሩ የነበሩት ሜኔንዴዝ ከሴኔቱ እንደሚሰናበቱ አስታወቁ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የግብጽ መንግሥትን ጨምሮ ለውጪ መንግሥታት ለመስራት ጉቦ በመቀበል ጥፋተኛ የተባሉት የኒው ጀርዚው ሴናተር ቦብ ሜኔንዴዝ ከሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልነታቸው ሊለቁ ነው።

ሴናተር ሜኔንዴዝ የሙስና ክሶች ከቀረቡባቸው በኋላ የሴኔት ወንበራቸውን እንዲለቁ ተደጋጋሚ ጥሪ ሲቀርብላቸው ቢቆይም፤ጥሪውን ለመቀበል ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ የሴኔቱ የስነ-ምግባር ኮሚቴ ሴናተሩ ከሴኔቱ የሚወገዱበትን አማራጭ ማጤን ሲጀምር ቦብ ሜንዴዝ ወንበራቸውን እንደሚለቁ ይፋ አድርገዋል።

በ16 የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ የተባሉት የቀድሞው የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር፤ የቅጣት ውሳኔ ሲተላለፍባቸው በርካታ ዓመታትን በእስር ሊያሳልፉ ይችላሉ።

የኳታር እና የግብጽ መንግሥታትን ለመርዳት ጉቦ የተቀበሉት ሜንዴዝ ጥቅምት 19/2017 ዓ.ም. የቅጣት ውሳኔ ይተላለፍባቸዋል።

ሴናተሩ ሙስና ተቀብለው የግብፅ መንግሥት በሚሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአሜሪካ መንግሥት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲያገኝ ረድተዋል ተብለዋል።

ሴናተሩ ከግብጽ መንግሥት ጋር የጥቅም ትስስር ካላቸው ግብፃውያን ከሆኑ የንግድ ባለቤቶች ጥሬ ገንዘብ፣ ወርቅ እና ቅንጡ መኪና ተብለዋል።

ሜኔንዴዝ የውጪ መንግሥታትን ፍላጎት ለማስፈጸም ከተቀበሏቸው ስጦታዎች መካከል 100ሺህ ዶላር የሚያወጣ ወርቅ እና ቅንጡ መርሰዲስ መኪና የተጠቀሱ ሲሆን፣ በመኖሪያ ቤታቸውም 480 ሺህ ዶላር ጥሬ ገንዘብ ተገኝቷል።

የ70 ዓመቱ ሴናተር በሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ከተባሉም በኋላ “ሕዝብን ለማገልገል የገባሁትን ቃል ኪዳን አላፈርስኩም” ብለዋል።

የሴናተሩ ጠበቆች ሜኔንዴዝ የተቀበሏቸው ስጦታቸዎች እንደ ጉቦ መታየት የለባቸውም ሲሉ ተከራክረዋል። ዐቃቤ ሕግ ሴናተሩ ለተቀበሏቸው ስጦታዎች ምላሽ ይሆን ዘንድ የዋሉት ውለታ ስለመኖሩ ማረጋገጫ የለውም ሲሉ ጠበቆች ሞግተዋል።

በዚህ የሙስና የወንጀል ክስ ትውልዳቸው ሌባኖስ የሆኑት የሴናተሩ ባለቤት ናዲን ሜኔንዴዝ ጭምር ተከሰዋል።

ሜኔንዴዝ ለኒው ጀርዚ ግዛት አስተዳዳሪ ፊል መርፊ ባስገቡት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸው ላይ ሴናተር ሆነው በሰጡት አገልግሎት እንደሚኮሩ እና የተላለፈባቸው የጥፋተኝነት ውሳኔን ይግባኝ እንደሚሉ አመላክተዋል።

ሜኔንዴዝ ጨምረውም፤ “ሴኔቱ ውድ ጊዜውን የእኔን ጉዳይ በመመልከት ጊዜውን እንዲያባክን አልፈልግም” ብለዋል።

ሜኔንዴዝ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ ምክር ቤት አባል ሆነው የተመረጡት እአአ 1993 ነበር። በሴኔቱ ደግሞ እአአ 2006 ላይ ወንበር አግኝተዋል።