ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኒውዮርክ ከንቲባን ክስ እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ከፍተኛ አቃቤ ህግ ከስራ ለቀቁ
በኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ኤሪክ አዳምስ የተጀመረውን የሙስና ክስ እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ የተሰጣቸው የማንሃተን ከፍተኛ አቃቤ ህግ ከስራ ለቀቁ።
በቅርቡ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሹመት ከፍ ያሉት ወግ አጥባቂዋ ዳኒየል ሳሱን "አስደንጋጭ እና አደገኛ ምሳሌ ይሆናል" በሚል ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ገልጸዋል።
የዳኒየል ከኃላፊነታቸው መልቀቅ እንዲሁም ተመሳሳይ እርምጃ የወሰዱ ቢያንስ ሁለት ሌሎች ከፍተኛ የፍትህ መስሪያ ቤት ባለስልጣናት ጋር ተደምሮ የትራምፕ አስተዳደር በፌደራል ህግ አስከባሪዎች ላይ እያደረጉት ያለው ስር ነቀል ለውጥ ስጋት መፍጠሩ ማሳያ ነው ተብሏል።
የኒውዮርክ ከንቲባ ኤሪክ መስከረም ወር ላይ ከቱርክ ዜጎች ከ100 ሺህ ዶላር የሚበልጥ ስጦታን በሙስና መልክ ተቀበለዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል። ከንቲባው የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
የከንቲባውን ጉዳይ ወደ ፍርድ ያመጡት በቀድሞው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተሾሙ ባለስልጣናት ናቸው።
ነገር ግን በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ፣ የትራምፕ ተሿሚ የሆኑት ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኤሚል ቦቭ፣ ዳኒየል ሳሱን እና የኒውዮርክ አቃብየነ ህግ በከንቲባው ላይ የጀመሩትን ክስ እንዲያቋርጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ኤሚል ቦቭ ለዚህ እንደ ምክንያትነት ያቀረቡት ከንቲባው የትራምፕ አስተዳደር ቁልፍ ግብ የሆኑትን "ህገወጥ ስደትን እንዲሁም አስከፊ ወንጀሎችን" የመግታት ስራቸውን ገድቦታል የሚል ነው።
ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ክሱን በተመለከተ አስተያየት ባይሰጡም ሆኖም ህዳር ወር ላይ የኒውዮርክ ከንቲባ ምርጫ በኋላ የፍትህ መስሪያ ቤቱ ክሱን እንደገና የመክፈት መብቱ የተጠበቀ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዳኒየል ክሱን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሲሆን ሐሙስ ዕለት ለኤሚል አለቃ አቃቤ ህግ ፓም ቦንዲ በላኩት ደብዳቤ ክሱን ለማቋረጥ "አሳማኝ ምክንያት አላየሁም" ብለዋል።
"ህጉ ክስን መሰረዝ ስለማይደግፍ እንዲሁም ኤሪክ አዳምስ የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች እንደፈጸሙ እርግጠኛ ስለሆንኩ ተገቢ ባልሆነ ምክንያት ክሱን ለመተው አልስማማም" ሲሉ በደብዳቤያቸው ላይ አስፍረዋል።
ዳኒየል ሳሱን ቢሯቸው ከተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ከከንቲባው ጠበቆች ጋር ከሁለት ሳምንታት በፊት መነጋገራቸውን ገልጸዋል። የከንቲባው ተወካዮች ደንበኛቸው የአስተዳደሩ ፖሊሲዎችን የሚያግዙት "ክሳቸው ከተሰረዘ ብቻ መሆኑን" ሃሳብ ማቅረባቸውን አቃቤ ህጓ ተናግረዋል።
የከንቲባው ጠበቃ የሆኑት አሌክስ ስፒሮ በበኩላቸው ደንበኛቸው ኢሚግሬሽንን ለማጠናከር በሚል ክሱ እንዲቋረጥ የተደረሰ ስምምነት የለም ብለዋል።
"ከትራምፕ አስተዳደር የተደረሰ ስምምነት የለም። እኛ ያቀረብነው ሃሳብ እንዲሁም የፍትህ መስሪያ ቤቱ ያቀረበልን ነገር የለም" ብለዋል ጠበቃው።
ተጠባባቂ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የዳኒየል ሳሱንን መልቀቂያ በተቀበሉበት ደብዳቤ ላይ "ክሱን ለማቋረጥ ግልጽ መመሪያ ቢሰጡም ፖለቲካዊ ዓላማ ያለውን ክስ ለመቀጠል ሞክረዋል" ሲል ከሰዋቸዋል።
በተጨማሪም በኤሪክ አዳምስ ክስ ላይ የተሳተፉ ሌሎች አቃብያነ ህግ እረፍት እንዲወጡ እንደሚደረግ፣ እንዲሁም ዳኒየል ሳሱንን ጨምሮ ሌሎችም ውስጣዊ ምርመራ እንደሚከፈትባቸው አስረድተዋል።