ዘለንስኪ ያለ ዩክሬን ተሳትፎ የተደረሰ የሰላም ስምምነትን አልቀበልም አሉ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ እና ሩሲያ የሚያቀርቡትን ማንኛውም የሰላም ስምምነት አገራቸው ካልተሳተፈችበት እንደማይቀበሉ የዪክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ አስጠነቀቁ ።

ዘለንስኪ ይህንን ያሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለመቋጨት የሚያስችል ንግግር ለመጀመር ቃል መግባታቸውን ተከትሎ ነው።

"እንደ ነጻ አገር ይህንን ልንቀበል አንችልም" ሲሉ ዘለንስኪ ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ፑቲን ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ጦርነቱን ለማቆም ጥሩ እድል እንዳለ ገልጸው ነበር።

ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶን) መቀላቀሏ "የማይሆን ነው" ያሉት ትራምፕ አክለውም አገሪቷ "ከወረራው በፊት ወደነበረችበት ድንበር መመለስ የማይመስል ነገር ነው" ብለዋል።

በቀጣዩም የጸጥታ ጉባኤ እየተካሄደባት ባለው የጀርመኗ ሙኒክ የሩሲያ እና የአሜሪካ ተወካዮች እንዲገናኙ ትራምፕ ሐሳብ አቅርበዋል።

"ሩሲያውያን ከኛ ተወካዮች ጋር አንድ ላይ ናቸው። በነገራችን ላይ ዩክሬናውያን ተጋብዘዋል። ከየትኛው አገር የትኛው ተወካይ እንደሚመጣ እርግጠኛ አይደለሁም ነገር ግን ከሩሲያ፣ ከዩክሬን እና ከአሜሪካ የመጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት ይሳተፋሉ" ብለዋል።

"ሩሲያውያን ባገኛቸው ደስ ይለኛል። እነሱን ዝም ብሎ ገለል ማድረግ ስህተት ይመስለኛል። ይሄ ሩሲያን የመውደድ ወይም ያለ መውደድ ጥያቄ አይደለም" ብለዋል።

በዚህ ዓመታዊው ጉባኤ የማትሳተፈው ሩሲያ ትራምፕ ባሉት ጉዳይ ላይ ወዲያውኑ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች። የዘለንስኪ አማካሪ ዲሚትሮ ሊቲቪን በበኩላቸው "በሙኒክ ከሩሲያውያን ጋር ሊደረግ የታሰበ ውይይት ያልተጠበቀ ነው" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ዘለንስኪ አርብ እለት በሙኒክ ከትራምፕ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ጋር ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘዋል።

በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ከትራምፕ ጋር በስልክ የተነጋገሩት የዩክሬኑ መሪ አገራቸው "ያልተሳተፈችበት ማንኛውንም ስምምነቶች" መቀበል እንደማትችል ተናግረዋል።

"አውሮፓውያኑ በድርድር ጠረጴዛው ላይ ሊገኙ" እንደሚገባ የተናገሩት ዘለንስኪ አገራቸው ቅድሚያ የምትሰጠው "የደህንነት ዋስትና" ማግኘትን እንደሆነ ለትራምፕ ነግረዋቸዋል ተብሏል።

በሌላ አነገጋር ዩክሬን የኔቶ አባል መሆን ለአጋር አገሮቻቸውም "ወጪ ቆጣቢ" አማራጭ እንደሚሆን የገለጹት ዘለንስኪ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።

"ጦርነቱን ለማቆም ዝግጁ ነኝ የሚሉትን የፑቲንን ቃል እንዳያምኑ የዓለም መሪዎችን አስጠንቅቄያለሁ" ሲሉም አክለዋል።

ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ብቻ ሳይሆኑ አውሮፓውያን አጋሮቻቸውም ይህንን የትራምፕ እና የሩሲያ የሰላም ስምምነት ለመድረስ ንግግር ላይ ለመድረስ ቃል የገቡትን ጉዳይ ተቃውመውታል። የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሌይ "ከዩክሬን ውጭ ስለ ዩክሬን ምንም አይነት ድርድር ሊኖር አይችልም። የዩክሬን ድምጽ የየትኛውም ንግግሮች ማዕከል መሆን አለበት" ብለዋል።