አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አወዳድሮ እንጂ በምደባ እንደማይቀበል አስታወቀ

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ

የፎቶው ባለመብት, WIKI

ታትሟል

በኢትዮጵያ አንጋፋው የትምህርት ተቋም የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ጀምሮ ተማሪዎችን አወዳድሮ እንጂ ከዚህ ቀደም እንደነበረው በምደባ እንደማይቀበል አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ይህን ያለው በአገሪቱ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተከትሎ ነው።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚክ ነጻነት እንዲረጋገጥ፣ ከፖለቲካዊም ሆነ ከአስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆነው የመማር ማስተማር ሥራዎችን ማካሄድ እንዲችሉ በሚል ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲዎች ለማቋቋም የሚያስችል አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በግንቦር 2015 ዓ.ም. መጽደቁ ይታወሳል።

በዚህም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ ሆኗል። ዩኒቨርሲቲው በዛሬው ማክሰኞ ነሐሴ 16/2015 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን የሚቀበለው በውድድር ብቻ ነው ብሏል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በመግለጫው ላይ፣ የራስ ገዝ አስተዳደር ውሳኔው የትምህርት ጥራትን በማሻሻል፣ ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን እና የዩኒቨርስቲው የአካዳሚክ እና የአስተዳደር ሙሉ ነፃነት ኖሮት በኃላፊነት ይሰራል ስለማለታቸው ዩኒቨርሲቲው በማኅበራዊ ገጹ ላይ አስታውቋል።

ከቀጣዩ 2016 ዓመት የትምህርት ዘመን ጀምሮ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ሚኒስቴር የመቁረጫ ነጥብ ያገኙ የቅድመ ምርቃ ተማሪዎችን አወዳድሮ እንደሚቀበል ተገልጿል።

ይህ ማለት ከዚህ ቀደም እንደነበረው 12ኛ ክፍል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን በማለፍ በምደባ ዩኒቨርሲቲውን መቀላቀል ቀርቶ፣ ተማሪዎች አንጋፋውን የትምህርት ተቋም መቀላቀል የሚሹ ከሆነ ተወዳዳሪ ሆነው የሚሰጣቸውን የመግቢያ ፈተና ማለፍ ይኖርባቸዋል።

ራስ ገዝ ዩነቨርሲቲ

ይህ የመንግሥት የትምህር ተቋማትን ራስ ገዝ የማድረጉ ውሳኔ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወሰነ በኋላ በወቅቱ ብዙ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

አንድ የትምህርት ተቋም ራስ ገዝ ሆነ ማለት ተማሪዎችን ያለመንግሥት ምደባ በራሱ የመግቢያ ፈተና አወዳድሮ የሚቀበል፣ የራሱን ሠራተኞች መቀጠር እና ማሰናበት የሚችል፣ ግዢን ጨምሮ የራሱን የፋይናንስ እንቅስቃሴ በራሱ የመምራት ነጻነት ይኖረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆናችውን የሚደግፉት ተቋማቱ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲስያስተዳድሩ ስለሚፈቅድ በአስተዳደርም ሆነ አካዳሚክ ነጻነት ይኖራቸዋል ይላሉ።

በትምህርት ተቋማቱ የሚሰሩ መምህራን እና ሌሎች ሠራተኞችም የተሻለ ክፍያን ማግኘት ይጀምራሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ራስ ገዝ የሆኑ የትምህር ተቋማት የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎች የማይቀመሱ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ስጋት ያላቸውም አሉ።

ተቋማቱ ራስ ገዝ ከሆኑ በኋላ ከመንግሥት የሚያገኙት የገንዘብ ድጋፍ የሚቋረጥ ከሆነ ዩኒቨርሲቲዎቹ የጎደለውን ገንዘብ ለማሟላት በሚያደርጉት ጥረት ገንዘብ ላላቸው ተማሪዎች ቅድሚያ ሊሰጡ እና ይህም ፍትሃዊነትን ሊያዛባ ይችላል በማለት አስተያየት የሚሰጡ ባለሙያዎችም አሉ።

ዛሬ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰጠው መግለጫ ላይ ተማሪዎችን አወዳድሮ የሚቀበለው በቅድመ ክፍያ ይሁን በወጪ መጋራት ሥርዓት የተባለ ነገር የለም።