መንግሥት ከአንዳንድ አገራት ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማጤን እገደዳለሁ አለ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፌደራል መንግሥቱ ሁለት አመት ከዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ላይ መሠረተ ቢስ ክሶች ከሚያቀርቡ አገራት እና ተቋማት ጋር ያለኝን ግንኙነት ለማጤን እገደደላሁ አለ።
የፌደራል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አገልግሎት ዛሬ ጥቅምት 18/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከፍ ያሉ የሐሰት ስም የማጥፋት ወንጀሎች ከአሁን በኋላ አልታገስም ብሏል።
የፌደራሉ መንግሥት “ኃላፊነት የጎደለውን የህወሓት ፕሮፖጋንዳ” እያስተጋቡ ናቸው ያላቸውን አገራት እና ተቋማት በስም አልጠቀሰም።
መንግሥት በአገሪቱ ላይ ያልተረጋገጡና ፖለቲካዊ ዓላማ ያላቸውን ክሶች እያቀረቡ ናቸው ካላቸውና በስም ካልጠቀሳቸውን መንግሥታትና ተቋማት ጋርም ያለውን ግንኙነት ለማጤን መገደዱን በዛሬው መግለጫው አትቷል።
መንግሥት ይህንን መግለጫ ያወጣው ጦርነቱ በተለያዩ ግንባሮች ተፋፍሞ ቀጥሏል በተባለበትና የሰላማዊ ሰዎች መገደልና መፈናቀል ሪፖርት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና የኤርትራ ኃይል ጥምር ጦር ወታደራዊ እርምጃቸውን ገትተው ለንጹኃን ደኅንነት እንዲጠብቁ አሳስቧል።
በተጨማሪም አሜሪካን ጨምሮ የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከሰሞኑ መጠየቃቸው ይታወሳል።
እነዚህ መግለጫዎች መውጣታቸውን ተከትሎ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች “ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል
የሰልፉ አዘጋጆች የምዕራባውንን “ያልተገባ ጣልቃ ገብነት የሚቃወምና ለአገሪቱ ሉዓላዊነትናየግዛት አንድነት መከበር በሁሉም መስክ ከመንግሥት ጎን መቆማችንን ለማረጋገጥ ነው።” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ አየርላንድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጻረሩ ድርጊቶችን እየፈጸመች ነው ስትል የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለአገሪቱ ጽፋ ነበር።
አውሮፓዊቷ አገር አየርላንድ በኢትዮጵያ ላይ “ያልተጠበቀ ደባ እየፈጸመች ነው” ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለአየርላንዱ አቻቸው ደብዳቤ ጽፈዋል።
“ህወሓትን በመደገፍ በፀጥታው ምክር ቤት ያላትን መቀመጫ በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር ግፊት እያደረገች ነው” በማለት፣ አገሪቱ ከዚህ “ኢትዮጵያን ከማጥቃት ድርጊቷ እንድትታቀብ” ደብዳቤው ጠይቋል።
አሜሪካን በተመለከተም ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያውን ጨምሮ ለመንግሥት ቅርበት ያላቸው መገናኛ ብዙሃን የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር “ከአሸባሪ ጋር በመወገን በኢትዮጵያ ላይ ጫና እያደረገ” ነው የሚሉ ሪፖርቶችን እያወጡ ነው።
መንግሥት በዛሬው መግለጫ አንዳንድ ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረ ዘመቻ ከፍተዋል ሲል ወቅሷል። ሆኖም አንዳንዶች ይህንን በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ስም ማጥፋት አምነው እንደሚታለሉ ጠቅሶ አንዳንዶች ግን ይህንን ውንጀላ ተጠቅመው ኢትዮጵያ እንድታጎበድድ ለማድረግ እየሞከሩ ነው ሲል ወቅሷል።
“ይህንን መሰል አጸያፊ ውንጀላ በማቅረብ የኢትዮጵያ መንግሥት በህወሃት ላይ እየወሰደ ያለውን የመከላከል እርምጃ እንዲቀይር የሚያስፈራሩ መስሏቸው ከሆነ ተሳስተዋል” ብሏል።
"አንዳንዶች ህወሃትን ለማዳን እየሰሩ ነው" ያለው መግለጫው ውንጀላና ስም ማጥፋት መሬት ላይ ያለውን እውነታ አይለውጠውም ብሏል።
አምስት ወራት የዘለቀውን የተኩስ አቁም ተከትሎ በተለያዩ ግንባሮች የቀጠለው ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዲቆም የተለያዩ ዓለም አቀፍ መንግሥታትና ተቋማት ጥሪ እያደረጉ ይገኛሉ።
ከቅርብ ቀናት በፊትም የትግራይ ኃይሎችንና የኢትዮጵያ መንግሥትን ለማወያየት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሰላም ንግግር የተጀመረ ሲሆን ከሰሞኑም አሜሪካ ይህንን ጥረት እንደምትደግፍ ገልጻለች።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ አሜሪካ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ዕልቂት የሆነው ጦርነት በሰላም ለመቋጨት የሚደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን መንግሥታቸው ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ሙሉ እና ንቁ ተሳትፎም በማድረግ የአፍሪካ ህብረትን እየደገፈ ነው ብለዋል።
ሆኖም ይህንን ግጭት ለመፍታት የሚያደናቅፉ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነን ብለዋል።
በተጨማሪም በሰሜን ኢትዮጵያ ያገረሸው ጦርነት በአስቸኳይ ካልቆመ ጠንከር ወዳለ እርምጃ እንደሚገቡ የአሜሪካ ባለስልጣን አስጠንቅቀዋል።
የአሜሪካ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሴናተር ቦብ ሜንዴዝ የተኩስ አቁም በሌለበት ሁኔታ ጦርነቱን ለማስቆም እና ለደረሱ ጥሰቶች ተጠያቂነት እንዲኖር ተጽዕኖ ይፈጥራል የተባለውን ረቂቅ ህግ ሴኔቱ እንዲያሳልፈው እገፋለሁ ከሰሞኑ ብለዋል።
ጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ በትግራይ ሰላማዊ ነዋሪዎችን ባልለየ መልኩ ጥቃት እየተፈጸመ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አውሮፓ ህብረት ሌሎች ተቋማትም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
በቅርቡም የትግራይ አንዳንድ ከተሞች በኢትዮጵያና በኤርትራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ ነዋሪዎች ስጋት እንዳደረባቸው አምነስቲ በቅርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል አጋር የሆነው የኤርትራ ጦር በሽራሮ ከተማ ከጳጉሜ 1፣ 2014 ዓ.ም- መስከረም 2/ 2015 ዓ.ም ባሉት ቀናት ኤርትራውያን ስደተኞችን ጨምሮ ቢያንስ 40 ነዋሪዎችን መግደሉንም አስታውቋል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው ቀናት በቀረው ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላማዊ ዜጎች ላይ መደፈር፣ ወሲባዊ ጥቃቶች፣ የዘፈቀደ ግድያ እና ረሃብ እንደ ጦር መሳሪያ ጥቅም ላይ መዋላቸውን የተመድ ሰብአዊ መብት ሪፖርት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።












