የምዕራባውያንን ‘ያልተገባ ጣልቃ ገብነት’ የሚያወግዝ ሰልፍ ተካሄደ

የፎቶው ባለመብት, EBC
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች“ለኢትዮጵያ እቆማለሁ ድምጼን አሰማለሁ” በሚል መሪ ቃል ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሄደ።
ይህ ሰልፍ የምዕራባውያንን “ያልተገባ ጣልቃ ገብነት” የሚቃወም እንደሆነ ዘገባዎች ይጠቁማሉ።
ሕዝባዊ ሰልፉ የተዘጋጀው በሙያ ማኅበራት፣ በሲቪል ማኅበራት እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎች እንደሆነ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የሰልፉን አዘጋጆች ጠቅሰው የወጡ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት “የሰልፉ አላማ ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቅናለአገሪቱ ሉዓላዊነትናየግዛት አንድነት መከበር በሁሉም መስክ ከመንግሥት ጎን መቆማችንን ለማረጋገጥ ነው።”
ይህ ሰልፍ የተደረገው ጦርነቱ በተለያዩ ግንባሮች ተባብሶ ቀጥሏል በተባለበትና የሰላማዊ ሰዎች መገደልና መፈናቀል ሪፖርት እየተደረገ ባለበት ወቅት ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ” የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም የኤርትራ መከላከያ ጥምር ወታደራዊ እርምጃቸውን ገትተው የንጹኃንን ደኅንነት እንዲጠብቁ እናሳስባለን” ብሏል።
በተጨማሪም ኤርትራ ጦሯን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ እና ሰብአዊ እርዳታ ለሚያሻቸው ሁሉ ያልተገደበ ድጋፍ በአፋጣኝ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል።
ከአሜሪካ በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ከሰሞኑ መጠየቃቸው ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Press Agency
“No More To Proxy War” “For Sustainable Peace Disarm TPLF” “We Are Lions In The Jungle” የሚሉ በእንግሊዝኛ የተጻፉ መፈክሮች በመስቀል አደባባዩ ሰልፍ ታይተዋል።
በተጨማሪም “ሉዓላዊነታችን ይከበር”፣ “የትግራይ ሕዝብ ወገናችን ነው”፣ “በሰብአዊ እርዳታ ስም ጣልቃ ገብነት ይቁም”፣ “በአንድ ሉዓላዊ አገር ሁለት ሠራዊት አይኖርም” የሚሉና ሌሎችም መፈክሮች ተስተውለዋል።
የፊታችን ሰኞ በአፍሪካ ኅብረት ሥር የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና የትግራይ አመራሮች የሰላም ውይይት እንደሚያካሂዱ ይጠበቃል።
ለአምስት ወራት የቆየውን ሰብአዊ ተኩስ አቁም ነሐሴ ላይ ተቀልብሶ ዳግመኛ ጦርነት ተቀስቅሷል።
ከሳምንታት በፊት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ይካሄዳል ተብሎ የነበረው የሰላም ንግግር መሸጋገሩን ተከትሎ በነበሩት ቀናት ውጊያው የቀጠለ ሲሆን፤ የፌደራሉ መንግሥት ሽረ እና አላማጣን መያዙ አይዘነጋም።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Press Agency
መንግሥት የኮረም ከተማንም እንደያዘ ቢናገርም፤ የትግራይ አመራሮች ግን ከተማዋ አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናት ብለዋል።
በቀጠለው ጦርነትም በርካታ ንጹኃን ሰዎች እንደተገደሉና እንደተፈናቀሉም ሪፖርቶች እየወጡ ይገኛሉ።
በመጪው ጥቅምት 24/2015 ዓ. ም. ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለመቶ ሺዎች መፈናቀል፣ ሚሊዮኖችን ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ከማድረግ ባሻገር ከባድ ቁሳዊ ውድመትን አስከትሏል።
የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ የአውሮፓ ኅብረት እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቀማት እና አገራት የእርስ በእርስ ጦርነቱ እንዲቆም፣ ያልተገደበ ሰብአዊ እርዳታ እንዲደርስ እንዲሁም መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጥሪ ማቅረባቸውን ቀጥለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Press Agency
ኢትዮጵያ ላይ ትኩረቱን ያደረገ እንደሚሆን ከተነገረው የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት አስቀድሞ፣ የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይና የደኅንነት ፖሊስ ከፍተኛ ተወካይ እንዲሁም የአውሮፓ ኮሚሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ጆሴፕ ቦሬል፤ “በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለው ስቃይና እንግልት እጅግ ይሰብራል” ብለዋል።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ቀውስ ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው” ሲሉ ያደረጉትን ንግግር የአውሮፓ ኅብረት እንደሚደግፈውም ጆሴፕ ቦሬል ጠቁመዋል።
ጉቴሬዝ ከቀናት በፊት “ማኅበረሰባዊ ትስስሩ እየተበጣጠሰ ነው። ንጹኃን ዜጎች ናቸው ዋጋውን እየከፈሉ ያሉት። በትግራይ ያለው ግጭት አሁኑኑ በቆም አለበት። የኤርትራ ኃይሎችም ከኢትዮጵያ መውጣት አለባቸው” ማለታቸው ይታወሳል።
ይህንን ንግግር እንደሚደግፉት የገለጹት ቦሬል፤ “ወቅቱ ሁሉም ወገን ለሰላም የሚቆምበት ነው” ሲሉ የአውሮፓ ኅብረትን አቋም አንጸባርቀዋል።












