አወዛጋቢው አንድሪው ቴት እና ወንድሙ ወደ ቤት ውስጥ እስር ተዛወሩ

አንድሪው ቴት እና ወንድሙ ትሪስታን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

አወዛጋቢው የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ አንድሪው ቴት እና ወንድሙ ትሪስታን ቴት የሮማኒያው ዳኛን ውሳኔ ተከትሎ ከእስር ቤት ወደ የቤት ውስጥ እስር ተዛወሩ።

በሮማኒያ ዋና ከተማ ቡካሬስት የሚገኘው ይግባኝ ሰሚ ፍርድቤት ባስተላለፈው ውሳኔ የእነቴት የእስር ቤት ቆይታ ለ30 ቀናት በሚዘልቅ የቤት ውስጥ እስር ተተክቷል።

ሁለቱ ግብር አበሮቻቸው ጆርጂያና ናጌል እና ሉአና ራዱም ከእስር ተለቀዋል።

ይሁን እንጂ አራቱም ግለሰቦች ለመውጣት የሕግ ፍቃድ ካልተሰጣቸው በስተቀር በሚኖሩበት ሕንጻ ውስጥ እንዲቆዩ ትዕዛዝ ተሰጥቷቸዋል።

የቴት ወንድማማቾች ቃል አቀባይ፣ ወንድማማቾቹ ከእስር በመለቀቃቸው በጣም ደስተኞች መሆናቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወንድማማቾቹ በቀረበባቸው የመድፈር፣ የሰዎች ዝውውር እና ወንጀለኛ ቡድንን አቋቁመዋል በሚል ክስ ከባለፈው ታኅሳስ ወር አንስቶ ታስረው ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።

ግለሰቦቹ ግን ድርጊቱን አልፈፀምንም ብለዋል።

የቴት ጠበቆች እንደ የቤት ውስጥ እስር ያለ ሌሎች የሕግ አማራጮች እያሉ ቴት በእስር ቤት እንዲቆይ መደረጉ አላስፈላጊና ከባድ ውሳኔ ነው ሲሉ ተከራክረዋል።

ቢቢሲ የተመለከተውና ሾልኮ የወጣ የፍርድ ቤት መረጃ፣ አካላዊ ጥቃት እየተፈፀመባቸው በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች በወር 10 ሺህ ዩሮ እንዲያገኙ መገደዳቸውን የተጎጂዎችን የምስክርነት ቃል ያትታል።

ከዚህም በተጨማሪ እዳዎችን እንደ ማስፈራሪያ መጠቀማቸውን የፍርድ ቤቱ መረጃ አመልክቷል።

በእነርሱ ላይ ምርመራው ከተጀመረበት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ጀምሮ ስድስት ሴቶች ጥቃት እንደተፈፀመባቸው በአቃቤያነ ሕግ ለይተዋል።

ሆኖም በወንድማማቾቹ ላይም ሆነ ከእነርሱ ጋር በታሰሩት ሁለቱ ግብረ አበሮቻቸው ላይ እስካሁን ምንም ዓይነት ክስ አልቀረበም።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2016 እንግሊዝ አሜሪካዊው የቀድሞ ኪክቦክሰር ቴት፣ ሴት ላይ ጥቃት ሲሰነዝር በሚያሳየው ቪዲዮ በማቅረቡ ምክንያት በብሪቲሽ ቴሌቪዥን ላይ ከሚቀርበው 'ቢግ ብራዘር' ሾው እንዲነሳ ተደርጓል።

አንድሪው ቴት በቀደመ የስፖርት ሕይወቱ ከአንዴም አራት ግዜ የኪክቦክስ ውድድር የዓለም ሻምፒዮና ቢሆንም አሁን ላይ ታዋቂ ያደረገው ሴቶችን በተመለከተ የሚሰጣቸው “አጸያፊ ፣ ጾተኛ እና አስነዋሪ” የተባሉት አስተያየቶቹ ናቸው።

አንድሪው ቴት ከዚህ ቀደም "ሴቶች ለሚደርስባቸው ወሲባዊ ጥቃት ኃላፊነቱን መውሰድ አለባቸው" በሚል ትዊተር ላይ ባሰፈረው ጽሑፍም በትዊተር ታግዶ የነበረ ሲሆን ማኅበራዊ ሚዲያው በኤሎን መስክ ሥር መግባቱን ተከትሎ ዳግም ወደ ማኅበራዊ ትስስር መድረኩ ተመልሷል።

ቴት ምንም እንኳን የማኅበራዊ ሚዲያዎች እገዳ ቢጣልበትም በሚያቀርባቸው ቅንጦት የተሞላበት የአኗኗር ዘይቤው እና በስፖርታዊ ሕይወቱ ስኬት በተለይ በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ዝናን አትርፏል።