ፑቲን ያቀረቡትን የገና በዓል የተኩስ አቁም ጥሪ ዩክሬን ውድቅ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን የጦር ግንባሮች ከዛሬ አርብ ጀምሮ ለ36 ሰዓታት የሚቆይ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ለመከላከያ ሚኒስትራቸው ትዕዛዝ ሰጡ።
ተኩስ አቁሙ ከ6፡00 ሰዓት ጀምሮ [በሞስኮ ሰዓት አቆጣጠር 12፡00 ሰዓት] እንደሚጀምር መርሃግብሩ ያሳያል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ዩክሬንም በዚህ ላይ መልስ እንድትሰጥ የጠየቁ ቢሆንም ኪዬቭ ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጋለች።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የተኩስ አቁሙ የአገሪቷን ጦር ግስጋሴ ለማስቆም የተደረገ ሙከራ ነው ብለውታል።
ክሬምሊን ያወጣችው መግለጫ፣ ፕሬዝዳንት ፑቲን መዋጋታቸውን እንዲያቆሙ ለወታደሮቻቸው ትዕዛዝ የሰጡት ጦርነቱ በመቆሙ ሳይሆን ከሩሲያ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መሪ የቀረበላቸውን ጥሪ ስለተቀበሉ መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ገልጿል።
ፓትሪያርክ ኪሪል ቀደም ብሎ ለኦርቶዶክስ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች አገልግሎቶችን እንዲካፈሉ ለገና የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበው ነበር።
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የገናን በዓል በጁሊያን አቆጣጠር ታኅሳስ 29 ያከብራሉ።
የክሬሚሊን መግለጫ እንደሚለው በፓትሪያርኩ የቀረበውን ጥሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት ፕሬዝዳንቱ ከዩክሬን ጋር ባሉ ግንባሮች ሁሉ ለ36 ሰዓታት የሚቆም የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለመከላከያ ሚኒስትሩ መመሪያ ሰጥተዋል።
ፑቲን ዩክሬንም በጉዳዩ ላይ መልስ እንድትሰጥ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ይህም ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች የገና በዓል ዋዜማን እና ነገ የሚከበረውን የገና በዓልን ማክበር ይችላሉ ብለዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ምሽት ላይ ባስተላለፉት ቪዲዮ፣ ሩሲያ የዩክሬን ጦር በምስራቅ ዶንባስ ግዛት እያደረገ ያለውን ግስጋሴ ለመግታት እና የሰው ኃይልና መሣሪያ ለመስገባት የተኩስ አቁሙን እንደ ሽፋን መጠቀም ትፈልጋለች ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም “ይህ ምን ጥቅም ይሰጣል። ኪሳራቸውን ነው የሚያባብሰው” ብለዋል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሮ ኩሌባ በበኩላቸው ሞስኮ ፕሬዝዳንት ዜለንስኪ ለሰላም ያላቸውን አቋም በተደጋጋሚ ችላ ብላለች ሲሉ ሩሲያ ታኅሳስ 24 ኼርሶንን ስትይዝ እና በአዲስ ዓመት ዋዜማ ጥቃት መፈጸሟ ሞስኮ በኃይማኖታዊ በዓላት ወቅት ግጭት ለማቆም ፍላጎት እንደሌላት ማሳያ መሆኑን አጣቅሰዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፑቲን “የተወሰነ መተንፈሻ ጊዜ" እየፈለገ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
የፖለቲካ ተንታኟ ታትያና ስታኖቫያ እንደሚሉት ክሬሚሊን በሰፊው በሚከበረው የሩሲያ ክብረ በዓል ላይ ሌላ የከፋ ኪሳራ እንዳይደርስባት ማረጋገጥ አለባት። ፑቲን በኦርቶዶክስ የገና በዓል ተመሳሳይ ውድቀት እንዲገጥማቸው አይፈልጉም ብለዋል።
ቀደም ብሎ የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲብ ታይፕ ኤርዶዋን ሁለቱ ወገኖች መደራደር እንዲችሉ ፑቲን በዩክሬን የተናጠል ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠይቀው ነበር።
ሩሲያ የተኩስ አቁም ማድረጓን ባስታወቀች ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ደግሞ ጀርመን አሜሪካን በመከተል ለዩክሬን የአየር መከላከያ ሚሳይል እንደምትሰጥ ቃል ገብታለች። ጀርመን ከአሜሪካ ጋር በጋራ ባወጡት መግለጫ ሁለቱ አገራት የጦር ተሽከርካሪዎችን ለዩክሬን እንደሚልኩ ገልጸዋል።
ፈረንሳይ በበኩሏ ረቡዕ ዕለት የጦር ተሽከርካሪዎች እንደምትልክ አስታውቃለች።
ኪዬቭ ከሩሲያ እየተፈፀመባት ያለውን ጥቃት ለመመከት ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደደረግላት በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርባለች።












