ከባድ አውሎ ነፋስ በሁለት የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ ቢያንስ 26 ሰዎችን ገደለ

አደጋው የደረሰው ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ደቡባዊ የአሜሪካ ግዛቶችን በመታው ከባድ አውሎ ነፋስ ምክንያት በሚሲሲፒ እና በአላባማ ውስጥ ቢያንስ የ26 ሰዎች ሕይወት ጠፋ።

በአሁኑ ወቅትም በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ፈልጎ የማዳን ጥረት እየተደረገ ሲሆን፣ የሚሲሲፒ ግዛትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎባታል።

በሚሲሲፒ ግዛት ውስጥ የምትገኘው ሮሊንግ ፎርክ የተባለችው ከተማ ከሞላ ጎደል የወደመች ሲሆን፣ ጎዳናዎች በከባድ አውሎ ነፋሱ ምክንያት ከጥቅም ውጪ በሆኑ መኪኖች፣ በቤቶች ፍርስራሾች እና በመስታወት ስብርባሪዎች ተሸፍነዋል።

ከባድ አውሎ ነፋሱ ግዛቶቹን የመታው ነዋሪዎች እንቅልፍ ላይ በነበሩበት እኩለ ሌሊት ላይ ስለነበረ የማስጠንቀቂያ ደወልን የሰማ አልነበረም ተብሏል።

አደጋው የደረሰው ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከአደጋው መትረፋቸውን ተአምር ነው ያሉት ፍራንሲስኮ ማክናይት የተባሉት ነዋሪም፣ በውድቅት ሌሊት የነቁት በከባዱ የአውሎ ነፋስ ድመጽ መሆኑን ገልጸው፣ የዚያን አይነት የነፋስ ድምጽ በሕይወታቸው ሰምተው እንደማይያውቁ ተናግረዋል።

ነፋሱ ከአምስት አስከ አስር ደቂቃ ብቻ መቆየቱን የሚናገሩት ግለሰቡ በመታጠቢያ ቤታቸው ውስጥ ባለ ገንዳ ውስጥ ተደብቀው ነበር የተረፉት። በአሁኑ ወቅት ቤታቸው ሙሉ ለሙሉ ፈርሶ የመታጠቢያ ቤታቸው ሁለት ግድግዳዎች ብቻ ባሉበት ቆመው ይገኛሉ።

የሚሲሲፒ አገረ ገዢ ቴት ሪቭስ በከባዱ አውሎ ነፋስ የተመቱ የግዛቲቱን ከተሞች ቅዳሜ ዕለት በመጎብኘት ነዋሪዎችን ያነጋገሩ ሲሆን፣ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ያለውንም ሁኔታ “አሰቃቂ” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸውታል።

ተጨማሪ ከባድ አውሎ ነፋስ አላባማን እና ጆርጂያን እሁድ ዕለት ይመታል ተብሎ የተተነበየ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ በመታቸው አካባቢዎች ከአደጋው የተረፉ ሰዎችን ፈልጎ የማዳን ጥረት እንደሚቀጥልም ተነግሯል።

አደጋውን ተከትሎ ከሚሲሲፒ የደረሳቸው መልዕክት “ልብ የሚሰብር ነው” ያሉት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን፣ የፌደራል መንግሥቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ለመደገፍ “የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል” ሲሉ ቃል ገብተዋል።