የ241 ዓመታት እስር ተፈርዶበት በ27 ዓመታት እስር የተፈታው አሜሪካዊ

የፎቶው ባለመብት, BOBBY BOSTIC
241 ዓመታት እስር ተፈርዶበት 27 ዓመታት በእስር ላይ ለቆየው ቦቢ ቦስቲክ ዓለም እንግዳ ሆናበታለች።
በዚህ ዓመት ኅዳር ወር ላይ የተፈታው ቦቢ ከሌላ ዓለም እንደመጣ እየተሰማው ነው።
ገመድ አልባ የጆሮ ማዳመጫዎችን አያውቅም።
በብሉቱዝ ስልክ መገናኘቱም አስደናቂ ሆኖበታል።
በአሁኑ ወቅት መንገድ ላይ ሰዎች ለምን ብቻቸውን ያወራሉም እያለም እየተደመመ ነው።
እጅዎን ሲያንቀሳቅሱ ውሃ እና ለስላሳ የሚያፈሱ ማሽኖችንም እንዲሁ እንደ ህጻን ልጅ ነው የተመለከታቸው። እውነት ነው ዓለም እሱ እስር ቤት ከገባበት ከአውሮፓውያኑ 1995 ጋር ስትነጻጸር በርካታ ጉዳዮች ተለውጧል።
ከሁሉም የገረመው ግን ያገኛቸው ሰዎች ነበሩ፤ መልዓክ ነው የመሰሉት።
“ሰዎች ሳገኛቸው ፈገግ ብለው በወዳጅነት መልኩ ነው የሚያናግሩኝ፤ እቃ ልገዛ ገብቼ ‘ጌታዬ ልረዳህ እችላለሁ?’ ይሉኛል” ይላል የ44 ዓመቱ ቦቢ።
“እስር ቤት የሚታየው የጭካኔ ፊት ባስ ሲልም ትንኮሳ ነው” ይላል።
በአሁኑ ወቅትም “ሃይ ሰላም ነው፤ እንዴት ነህ?” የሚለውንም ንግግር ለመለማመድ እየሞከረ ነው።
“ውጭ ሁሉ ነገር ጥሩ ነው። ሰዎች ሲያዩህ ፈገግ ይላሉ። ህጻናት እጃቸውን ያውለበልባሉ። ሕይወት እንዲህ ነው መሆን ያለበት። ነገሮች እንደዚህ መሆን አለባቸው” ይላል።
ለ27 ዓመታት ያህል ስር በሰደደ ተቋማዊ ጥቃት ለተጎዳ ግለሰብ ሕይወትን መላመድ ከባድ እንደሆነ መገመት ይቻላል።
“ከባድ አይደለም። ምክንያቱም ሁልጊዜም ውስጥህ በሰብዓዊነት እንዲንከባከቡህ ይፈልጋል። ያንን ሰብዓዊ ግንኙነት ትፈልጋለህ። ያ ሕይወት ነው፣ ውበት ነው፣ ሰው የመሆን ደስታ ነው” ይላል።
10 ሺህ ምሽቶችን በአንዲት ክፍል ተቆልፎበት ካሳለፈ በኋላ የአውሮፓውያኑ ኅዳር 8/2022 የመጨረሻ ምሽቱም ሆነች። የመጨረሻዋን ሌሊት መተኛት አልቻለም፤ መቼ ይነጋ ይሆን? በሚል ነበር ያሳለፈው።
የነበሩትን እቃዎች ለታራሚዎቹ አከፋፍሎ የጽህፈት መኪናውን ብቻ ነበር የያዘው።
ሁሉም ነገር ህልም ህልም ነበር የመሰለው።
ጠዋት ላይም 27 ዓመታት የለበሳትን ግራጫማ የእስር ቤት የደንብ ልበሱን አውልቆ ሰማያዊ ሱፍ አጠለቀ።
“አዲሱን የሕይወቴን ምዕራፍ የሚወክል ልብስ እንደሆነ ተሰማኝ” ይላል።
ከሃያ አምስት ዓመታት በፊት ዳኛ ኤቭሊን ቤከር “በእስር ቤት እንደሚሞት” ነግራው ነበር። ነገር ግን በዚያች ኅዳር ጠዋት 1 ሰዓት ተኩል ነጻነቱ ታወጀ።
ፊቱ በፈገግታ ተሞልቶም ነበር። ልክ ሊወጣ ሲልም አንዲት ጥቁር ኮፍያ ያጠለቀች ሴት ልታቅፈው ተጠጋች። ይህችም ዳኛ ኤቭሊን ቤከር ነበረች።
ከዳኛዋ ጋር ከእስር ቤት ውጭ በመተቃቀፍ የተጠናቀቀው ጉዞ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 1995 ነበር።
የ16 ዓመቱ ቦቢ እና ጓደኛው ዶናልድ ሃትሰን ጂን ጠጥተው ማሪዋና ካጨሱ በኋላ ዘረፋ ፈጸሙ። የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ ለችግረኞች ስጦታ ሲሰጡ ከነበሩ ግለሰቦች ሰረቁ። ጉዳት ባያደርሱም ሽጉጥ ተኮሱ። ሽጉጥ ደግነው ከአንዲት ሴት መኪና ወሰዱ።
ቦቢ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ ካመነ ቅጣቱ የ30 ዓመት እስር ሊሆንለት እንደሚችል ጥያቄ ከፍርድ ቤት ቀርቦለት ነበር። ይግባኝም መጠየቅ ትችለላህም ተብሎ ነበር። እሱ ግን ይህንን ስምምነት ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም። ዳኛ ኤቭሊን በ17 ወንጀሎች የተለያዩ ቅጣቶች የፈረዱበት ሲሆን ተደምሮም 241 ዓመት ተወሰነበት።
በአውሮፓውያኑ 2018 ቢቢሲ ቦቢን ለመጀመሪያ ጊዜ ቃለ መጠይቅ ሲያደርግለት የተስፋ ጭላንጭል እንዳለው ተናግሮ ነበር።
ለዚህም ምክንያቱ በአውሮፓውያኑ 2010 የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታዳጊዎች የፈጸሙት የግድያ ወንጀል ካልሆነ ያለ ይግባኝ የዕድሜ ልክ ሊታሰሩ አይችሉም የሚል ውሳኔም አሳለፈ። በአውሮፓውያኑ 2016 እንደ ቦቢ ያሉ ጉዳዮችም መታየት እንደሚችሉ እርግጥ ሆነ።
ነገር ግን የሚዙሪ ግዛት ቦቢን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አልነበረም። ግዛቲቷ ቦቢ የእድሜ ልክ እስራት ሳይሆን የተፈረደበት፤ በበርካታ ወንጀሎች በርካታ ዓመት ነው የተበየነበት ስትል ተከራከረች። ይባስ ብሎ እርጅና ሲጫጫነው ይግባኝ መጠየቅ ይችላል አለ።
ቢቢሲ በአውሮፓውያኑ 2018 ከቦቢ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ ከአንድ ወር በኋላ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቦቢን ይግባኝ ውድቅ አደረገ። ለምን እንደሆነም አልገለጸም።
“ሌሎች ቢሆኑ ተስፋ ይቆርጡ ነበር። አንዴ ይግባኝ ውድቅ ከተደረገ ከዚያ የሚቀየር ነገር አይኖርም” ይላል ቦቢ።
ነገር ግን ቦቢ ተስፋ አልቆረጠም። ወደ ራስ አገዝ መጻህፍቶቹ ተመለሰ። ከእነዚህም መካከል የናፖሊዮን ሂል አድናቂ ነው። ጽሁፍ መጻፍ ጀመረ። ተስፋውም ሳይጨልም ለዓመታት ቆየ።
የሚዙሪ ግዛት አዲስ የሕግ ማሻሻያ አወጣች። ይህም በልጅነታቸው ወይም በታዳጊነታቸው ረጅም ዓመታት እስር ለተፈረደባቸው ታራሚዎች ይግባኝን እንዲሁም ይቅርታን የሚፈቅድ ነው።
ሆኖም እስከ 2021 ድረስ በሚዙሪ ሕግ አውጪ ክፍል አልጸደቀም ነበር።
“ብዙም እምነት አልነበረኝም” የሚለው ቦቢ “አብዛኛውን ጊዜ ሕግ በጥር ወይም በየካቲት ካልጸደቀ ከዚያ በኋላ የማለፍ ዕድል አልነበረውም” ይላል።
እናም በዚያ ወቅት ከአንድ የብዕር ጓደኛ ደብዳቤ ደረሰው።
እሱም 'ሚዙሩ ኢንዲፔንደንት' በተባለ ጋዜጣ ላይ የወጣ አንድ ጽሁፍ ነበር በኢሜይል የተላከለት። ይህም ኢሜይል ሕጉ እንደጸደቀ የሚያትት ነበር። ተዓምር ነበር።
የግዛቲቷ አስተዳዳሪ ሕጉ ላይ ፈርሞ ያጸድቀው ይሆን? የሚለው ሌላ ጥያቄ ነበር። አስተዳዳሪው ማይክ ፓርሰን ፈረሙበት። ለዚህ ሕግ ምስጋና ይግባውና ቦቢ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ለይግባኝም ሆነ ለምህረት ብቁ ሆኑ።
“ነገር ግን ምን እንደምጠብቅ አላውቅም ነበር” የሚለው ቦቢ፣ እንደገና ችሎት ቀርቦ አንድ ተወካይ እንዲመሰክርለት ማቅረብ ይችላል። ቦቢም ማንን እንደሚጠይቅ ሲያስብ፣ በእስር ቤት እንደሚሞት የነገረችውን ዳኛን አስታወሰ እና አሷን ጠየቀ።

የፎቶው ባለመብት, ACLU
ኤቭሊን በአውሮፓውያኑ 1983 በሚዙሪ ግዛት የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ዳኛ ሆና ነበር የተሾመችው። ጡረታ ከወጣች በኋላም በ2010 በታዳጊዎች እና በአዋቂዎች አዕምሮ መካከል ስላለው ልዩነት ስታነብ ነው የቦቢን ፍርድ እንደገና መመልከት የጀመረችው።
በ25 ዓመት የሥራ ዘመኗ የምትጸጸትበትም ብቸኛ ብይን እንደሆነም ትናገራለች። በ2018ም በዋሽንግተን ፖስት ላይ ቦቢ ላይ የተፈረደው ቅጣት “የተሳሳተ” እና “ኢ-ፍትሐዊ” ነበር በማለት ጻፈች። ከአንድ ወር በኋላም ለቢቢሲ ተመሳሳይ መልዕክት አስተላለፈች።
ታዲያ በይቅርታ ችሎቱ ላይ ምን አለች?
“ቦቢ የ16 ዓመት ልጅ ታዳጊ ቢሆንም እኔ ያየሁት እንደ ትልቅ ጎልማሳ ሰው ነበር። ይህ ስህተት ነበር” ስትልም ተናገረች።
“ከቦቢም ሆነ ከእህቱ ጋር ተቀራርበናል። በዓመታትም ከረባሽ ታዳጊነት እንዴት ወደ አሳቢ፣ ደግ አዋቂ ሰውነት እንደተቀየረ አይቻለሁ” ብላለች።
ከዳኛ ኤቭሊን በተጨማሪ ጉዳት አድርሶባቸዋል የተባሉትም ግለሰቦች ቦቢን በመደገፍ ጻፉ።
“ወደኋላ መመለስ ብችል ኖሮ ሌላ ብያይ አስተላልፍ ነበር” ብላለች ዳኛዋ።
የይቅርታ ጉዳዩ ከተሰማ ከአንድ ወር በኋላ ቦቢ ነጻ ተባለ።
“ገና፣ አዲስ ዓመት እና የትኛውም በዓል ተደራርበው አንድ ቀን የሆኑ ነው የመሰለኝ። ማልቀስ ጀመርኩ። ቦቢ ነጻ ተባለ” ብላለች።
ቦቢ ከዳኛ ኤቭሊን፣ ከጓደኞቹ፣ ከዘመዶች እና ከደጋፊዎች ጋር ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእስር ቤት ውጭ ምግብ ለመብላት ሄደ። ለ24 ዓመታት ያህል ሥጋም ሆነ የወተት ተዋጽኦዎችን ያልተመገበው ቦቢ የመጀመሪያው ምግቡ የሜክሲኮው ታኮ ነበር።
ሆኖም ታመመመ።
“መኪና ውስጥ ገብቼ አስመለሰኝ። በእስር ቤት 27 ዓመታት ለተወሰነ ሰው በመኪና መንቀሳቀስ ለካ ከባድ ነበር” ይላል።
ከህመሙ ካገገመ በኋላ ወዳደገበት እና እህቱ ወዳለችበት ሴንት ሉዊስ ከተማ አመራ። በአንድ ቀንም ከአራት መቶ በላይ ሰዎች ሊቀበሉት ወጡ።
“በአካባቢው ተሰልፈው ነበር። የአጎት ልጅ፣ የአክስት ልጅ፣ አክስት፣ ጓደኛ፣ ማለቂያ አልነበረውም። እስከ ሌሊት ስምንት ሰዓት ሰዎችን ስገናኝ ነበር” ይላል።
በአሁኑ ወቅት ቦቢ እና እህቱ ዲር ማማ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት አላቸው። ይም በሴንት ሉዊስ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ምግብ፣ መጫወቻ እና ሌሎች ድጋፎችን ይሰጣል። ድርጅቱ የተሰየመው በሟች እናቱ ዳያን ስም ነው።
ስለ እናቱ ሲናገርም “ብዙ ባይኖራትም፣ ለሰዎች ቸር ነበረች፤ ያላትን ትሰጥ ነበር” ብሏል። በከተማው የታዳጊዎች ማረሚያ ማዕከልም በየሳምንቱ ሐሙስ የጽሁፍ አውደ ጥናት ይሰጣል። እንደ በጎ አድራጎቱ ይህም የበጎ ፈቃድ ሥራ ነው።
ኑሮውን ለመደጎም ከመጽሐፍቶቹ ሽያጭ ነው ገንዘብ የሚያገኘው። በአማዞን ላይ ሰባት መጽሐፎች ያሉት ሲሆን፣ ሁሉም በእስር ቤት እያለ የጻፋቸው ናቸው። አልፎ አልፎም ንግግሮችን ያቀርባል። ከዚያም ከሚያገኘው ገንዘብ ነው ባለ አንድ መኝታ የሆነችውን የቤቱን ኪራይ የሚከፍለው።
የሚያገኘው ገንዘብ ብዙም አይደለም። የሙሉ ጊዜ ሥራ በማኅበረሰብ አገልግሎት ወይም ወጣቶችን በማነቃቃት ዘርፍ ማግኘት ህልሙ ነው። ምንም እንኳን የሚያገኘው ገንዘብ እዚህ ግባ ባይባልም ለውጭው ዓለም ያለው አድናቆትም ሆነ ምስጋና አልቀነሰም።
“አሁንም ከአንዳንድ ነገሮች ጋር እየታገልኩ ነው” የሚለው ቦቢ “ከዚያ ውጪ ግን እዚህ ያለው ሕይወት ውብ ነው። በየቀኑ ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው። ከማቀዝቀዣዬ ፈልጌ የምመርጠውን እጠጣለሁ። በመታጠቢያ ገንዳዬም እታጠባለሁ። ሁሉ ነገር ግሩም ነው” ይላል።
ቦቢ በሕይወት ሁለተኛ ዕድል አግኝቷል። ከእሱ ጋር አብሮ የታሰረው ዶናልድ ሃትሰን ዕድለኛ አልነበረም። ጥፋተኛ ነኝ ብሎ 30 ዓመታት የተፈረደበት ዶናልድ በ2018 እስር ቤት ሳለ ነበር ሕይወቱ ያለፈው። ከፍተኛ መጠን ያለው መድኃኒት ወስዶ እንደሞተ በምርመራ የተረጋገጠ ሲሆን፣ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ለይግባኝ እና ለይቅርታ ብቁ ይሆን።












