ተሰርቀው በወጡ ፎቶዎቿ በርካታ ወንዶች የተጭበረበሩባት ሴት

ቫኔሳ ከእርሷ ጋር የፍቅር ግንኙነት እንዳላቸው ከሚያምኑ ወንዶች በየቀኑ መልዕክቶች ይደርሷታል። አንዳንዶች እንዲያውም ሚስታቸው እንደሆነች ነው የሚያስቡት።
የሚናደዱ፣ ግራ የሚጋቡም አሉ።
አንዳንዶቹ ለቀን ወጪዋ፣ ለሕክምና እና ዘመዶቿን ለመርዳት ገንዘብ እንደላኩላት በመግለጽ ገንዘባቸውን እንድትመልስላቸው ይጠይቋታል።
ይህ ሁሉ ግን ሐሰት ነው። ለቫኔሳ የተላከ ገንዘብም ሆነ የተፈፀመላት ክፍያ የለም። እንዲያውም እነዚህን ወንዶች ጭራሽኑ አታውቃቸውም።
ሆኖም ቫኔሳ በመዝናኛው ዘርፍ ላይ በቆየችባቸው ጊዜያት የተነሳቻቸው ፎቶዎች እና የተቀረጸቻቸው ቪዲዮዎች ከአውሮፓውያኑ 2000 አጋማሽ አንስቶ ለማጭበርበር ጥቅም ላይ ውለዋል።
እውነተኛ ያልሆነ በበይነ መረብ ላይ የተፈጠረ ስብዕናን በመጠቀም የማጭበርበር ዘዴ (ካትፊሽንግ) በርካቶች በቫኔሳ ምስል አሊያም አምሳያ ተታለው ገንዘባቸውን ተዘርፈዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮችንም አጥተዋል።
ቫኔሳ ከእነዚህ በርካታ ወንዶች የሚጎርፉላት መልዕክቶችም ገንዘባቸውን ስለማጣታቸው እና ሕይወታቸው አደጋ ላይ ስለመውደቁ የሚያትቱ ናቸው።
በየዕለቱ የሚደርሷት መልዕክቶችም ቫኔሳን ለድብርት አጋልጠዋታል።
“ድብርት ውስጥ መግባት እና ራሴን መውቀስ ጀመርኩ። ምን አልባት ፎቶዎቼ ባይለቀቁ ኖሮ እነዚህ ወንዶች ሊጭበረበሩ አይችሉም ነበር” ትላለች ቫኔሳ።
ቫኔሳ ለስምንት ዓመታት ያህል በወሲብ ፊልም ሞዴልነት (ካምገርል) ሰርታለች። ከኮምፒዩተር ጋር በተገናኘ እና ኦንላይን ምስልን በሚያሳይ የቪዲዮ ካሜራ (ዌብካም) በመጠቀም ግልጽ የሆኑ ምስሎቿን በቀጥታ ታሰራጭ ነበር።
ታዲያ ይህንን ሥራ ስትጀምር ሃፍረት ይሰማት ስለነበር ‘ጃኔሳ ብራዚል’ የሚል ስም ለመጠቀም ወሰነች።
“ይህ ስም ትክክለኛዋን እኔን አይገልጽም። በቃ ጃኔሳ ነኝ! እንደዚያ በመሆኑ አላፍርም ብዬ አሰብኩ” ትላለች ሌላ ስም ለመጠቀም የወሰነችበትን ምክንያት ስታስረዳ።
በፈጠረችው ስም ላይ ብራዚል የሚለውን መጠሪያ ያስከተለችውም ብራዚል ውስጥ ስለተወለደች ብቻ አይደለም። ብራዚል የሚለው ቃል በኢንተርኔት ላይ ከሚፈለጉ ስሞች መካከል አንዱ በመሆኑም ጭምር እንጂ።
ይህም አውጥታ አውርዳ በማስተዋል የወሰነችው ውሳኔ ነበር።
አሁን ግን ይህንን ስም አብዝታ ትጠላዋለች። በእርግጥ በፍጥነት ዝነኛ እንድትሆን ረድቷታል።
ለተወሰነ ጊዜ ሁኔታዎች ለቫኔሳ ጥሩ ነበሩ። ቫኔሳ ከአድናቂዎቿ ጋር ባላት ግንኙነት ትደሰት ነበር።
እርሷን ለማየት እና ከእርሷ ጋር ለመገናኘት በደቂቃ እስከ 20 ዶላር ይከፍሏታል።
“እነርሱን ማስደሰት፣ ከእነርሱ ጋር መጫወት እፈልጋለሁ። ከዚያ ግን እነሱ በአጭበርባሪዎች ይጠመዳሉ” ትላለች።
ቫኔሳ በሥራዋ የመጀመሪያ ጊዜያት በዓመት አንድ ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ታገኝ እንደነበር ትናገራለች።
የራሷ ድረ ገጽ፣ ስኬታማ የሆነ መለያ ብራንድ እንዲሁም በኦንላይን ከፍተኛ እውቅና ነበራት።
ይሁን እንጂ በ2016 ስሟ ላይ ጥቁር ጥላ አጠላበት።
ከሚዲያው ራሷን አገለለች።
ቢቢሲ እንኳን በአሜሪካ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ በሚገኘው አፓርታማዋ አግኝቶ ያነጋገራት ከወራት ፍለጋ በኋላ ነበር።
ቫኔሳ፣ በኦንላይ ከምትሰራው ሥራ የጠፋችው አጭበርባሪዎችን ለማስቆም በማሰብ እንደሆነ ገልጻለች።
“ከዚህ በኋላ አጭበርባሪዎች የእኔ የሆነን ምንም ነገር እንዲጠቀሙ አቅም አልሰጣቸውም” ትላለች።

ቫኔሳ አጭበርባሪዎቹ የእርሷን ምስል ይጠቀሙ እንደነበር ያወቀችው ዘግይታ ነው።
አንድ ቀን አንድ ግለሰብ በቀጥታ በሚሰራጭ ፕሮግራሟ ላይ ገብቶ የእርሷን ፎቶ ለጠፈ። ግለሰቡ ባሏ እንደነበር እና የወሲብ ፊልም ሞዴልነትን ለማቆም ቃል ገብታለት እንደነበርም አስተያየቱን ጻፈ።
ቫኔሳ ይህ ቀልድ ነበር የመሰላት። በዚህ ግራ የተጋባችው ቫኔሳ፣ ግለሰቡ ኢሜይል እንዲያደርግላት ጠየቀችው።
ከዚያ በኋላ ግን በምታቀርበው ፕሮግራሞቿ ላይ ሁሉ አስተያየቶችን በመጻፍ ማንነቷን እንድታረጋግጥ የሚጠይቁ ተመሳሳይ ታሪክ ያላቸው ተጎጂዎች መጉረፍ ጀመሩ።
አጭበርባሪዎችም ግራ የሚያጋቡ የጓደኝነት ጥያቄዎች መላክ ያዙ።
ያለማቋረጥ የሚደርሷት አስተያየቶች እና የኢሜይል መልዕክቶች በጣም አስጨነቃት። በሥራዋ ላይም ተፅዕኖ ማሳደር ጀመረ። “ቅዠት ነበር” ትላለች ቫኔሳ ስለሆነው ስታስታውስ።
“ለእነዚህ ወንዶች በጣም ነው ያዘንኩት። ግን ምን ማድረግ ነበረብኝ?” ስትልም ትጠይቃለች።
መጀመሪያ ላይ ለሚላኩላት ኢሜይሎች መልስ መስጠት ጀምራ ነበር። ይህን ለማድረግ በአንድ ቀን ውስጥ ሰዓታት ይወስዱባታል።
በወቅቱ ባለቤቷ እንዲሁም ሥራ አስኪያጇ የነበረው ግለሰብ እርዳታ ታክሎበት እነዚህን መልዕክቶች መከታተል ጀመረ።
እርሱም ሆነ ቫኔሳ፣ ወንዶቹ ላጡት ገንዘብ ተጠያቂ አለመሆናቸውን ለተጭበርባሪዎቹ ማስረዳት ያዘ።
“እነዚህ ወንዶች ሁሉ የላኩትን ገንዘብ ብቀበል ኖሮ አሁን ላይ ቢሊየነር እሆን ነበር እኮ! እዚህ ትንሽ አፓርትመንት ውስጥ አልገኝም ነበር” ትላለች ቫኔሳ።
ቫኔሳ ሴቶችን መንከባከብ መፈለግ የወንዶች ተፈጥሮ እንደሆነ ታስበላች። በአካል ለማያውቁት ሰው ገንዘብ መላከቸውም ለዚህ ባህሪያቸው አንዱ ማሳያ እንደሆነ ትናገራለች።
“ገንዝብ ባይኖራቸው እንኳን ገንዘብ ለመስጠት ፈቃደኛ ናቸው። ለመወደድ ሲሉ ብቻ!” ትላለች።
በጃኔሳ ፍቅር የወደቀው ሮቤርቶ
በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኘው ጣሊያናዊው ሮቤርቶ ማሪኒ በሐሰተኛዋ ጃኔሳ ተጠምዶ ነበር።
ራሷን ሃናህ ብላ የምትጠራ ወጣት በሳርዲኒያ ደሴት ለጀመረው የእርሻ ሥራ ያላትን አድናቆት በመግለጽ በፌስቡክ መልዕክት በመላክ ነበር ትውውቁን የጀመረችው።
ከሦስት ወራት በኋላም ፎቶዎችን መላላክ ጀመሩ። ከዚያም የፍቅር መልዕክቶችን መለዋወጣቸውን ቀጠሉ።
እንዲህ እንዲህ እያለች ገንዘብ መጠየቅ ጀመረች።
መጀመሪያ አካባቢ ስልኬ ተሰበረ ዓይነት ምክንያቶችን በመስጠት አነስተኛ ገንዘብ ነበር የምትጠይቀው። ከዚያ ግን ብዙ ገንዘብ መጠየቅ ጀመረች። ፈታኝ ሕይወት እንዳሳለፈች በመግለጽ ወደ መዝናኛው ዓለም በመግባት ሕይወቷን ለመምራት እንደተገደደች ትገልጽለት ጀመር።
ሮቤርቶ ያሳለፈችውን ሲሰማ የአባትነት ስሜት ተሰማው። ሐዘን ውስጡን ሰርስሮት ገባ። ከገባችበት ሕይወት ሊታደጋት ፈለገ። ሆኖም በአካል ተገናኝተው እና አውርተው ስለማያውቁ ስጋት አደረበት።
ስልክ ለመደዋወል ቀጠሮ በያዙ ጊዜ ስልኳ ይቋረጣል አሊያም በደወለ ጊዜ የሆነ አንድ ነገር ይፈጠራል።
በዚህ ግራ የተጋባው ሮቤርቶ ስለሃናህ ለማወቅ በኦንላይን ስሟን እየጻፈ ማፈለግ ጀመረ። በፍለጋው በሺዎች የሚቆጠሩ የሃናህን ቪዲዎች እና ምስሎችን አገኘ። ምስሎቹ ከላከችለት በበለጠ ሰውነቷን በግልጽ የሚያሳዩ ነበሩ።
ሮቤርቶ ፍቅራቸው እውን ሆኖ ስለተሰማው ግንኙነታቸውን ሊያወሳስበው ይችላል በሚል እውነተኛ ማንነቷን መግለጽ አልፈለገች ይሆናል ብሎ አሰበ።
ሮቤርቶ አንድ ቀን በጃኔሳ ብራዚል በቀጥታ በሚሰራጭ የኦንላይን ፕሮግራም ላይ ተሳተፈ።
“አንቺው ራስሽ ነሽ?” ብሎ በውስጥ መስመር መልዕት ላከ። ነገር ግን ያገኘው የፈለገውን መልስ አይደለም። እርሷን ለማየት በደቂቃ እየከፈለ ስለነበር ብዙም ሳይቆይ ወጣ።
እውነቱን ለማወቅ ሮቤርቶ ኢሜይል አደረገላት።
ቢቢሲ ከቫኔሳ ጋር ቆይታ ባደረገበት ወቅት፣ ቫኔሳ የኢሜይል የመልዕክት ቋቷን ወደ ኋላ ተመልሳ ስታይ የሮቤርቶን መልዕክት በሺዎች ከሚቆጠሩ መልዕክቶች መካከል አግኝታዋለች።
እንደአውሮፓውያኑ በ2016 “ሰላም፣ ከእውነተኛዋ ጃኔሳ ብራዚል ጋር ማውራት እፈልጋለሁ” ሲል ጽፏል።
እሷም ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ “እውነተኛዋ ጃኔሳ ብራዚል ነኝ” ስትል መልሳለታለች።
ከዚህ በፊት አውርተው ያውቁ እንደሁ ለማረጋገጥ ጥቂት ጥያቄዎችንም አቅርቦላት ነበር።
ነገር ግን ይህን የኢሜይል መልዕክት ልውውጥ ያደረጉት ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ያላቸውም ብቸኛ አድራሻ ይኸው ነው።
በዚህ ግን አላበቃም።
ሮቤርቶ በአጭበርባሪዎች ወጥመድ ውስጥ ገብቷል። እርሱ እንደሚለው በአራት ዓመታት ውስጥ 250 ሺህ ዶላር ያህል ገንዘብ ልኮላቸዋል። ለሥራው ያጠራቀመውን ገንዘብ አሟጦ፣ ከጓደኞቹ እና ከቤተሰቦቹ እየተበደረ ልኳል። ከዚህ አልፎም ከባንክ እስከመበደርም ደርሷል።

ቢቢሲ ሮቤርቶን ያገኘው ሌሎች የጃኔሳን የተሰረቁ ፎቶች በመጠቀም በተከፈቱ ሐሰተኛ አካውንቶች (ገጾች) ከመጭበርበር እንዲጠነቀቁ በለጠፋቸው ማስጠንቀቂያዎች ነበር።
የሚገርመው ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላም ሮቤርቶ ከእውነተኛዋ ጃኔሳ ጋር ጥልቅ የሆነ ግንኙነት እንዳለው በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያምናል።
በበይነ መረብ አማካይነት የሚደረጉ የፍቅር ግንኙነቶች ላይ የተመሠረቱ ማጭበርበሮችን ያጠኑት በፊላደልፊያ የወንጀል ፍትሕ ባለሙያ ዶ/ር አንሹል ሬጊ፣ “ሮቤርቶ የተሰማው የስኬታማ ማጭበርበር ምልክት ነው” ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ተጎጂዎችን ለማታለል፣ ምስሎችን እና መረጃዎችን ለመለዋወጥ እንዲረዳ መልዕክቶች ብዙ ጊዜ የሚላኩት በቡድን በሚሰሩ የወንጀል ኔትዎርኮች ነው።
እነዚህ አጭበርባሪዎች ሊያጋልጣቸው የሚችሉ የስልክ ግንኙነቶችን ለማቋረጥ እና ሰበቦችን ለመደርደር የሚጠቀሙበትን መመሪያዎች ምሳሌ እንዳገኙም ዶ/ር ሬጊ ተናግረዋል።
“አጭበርባሪዎች መመሪያ ተከትለው ነው የሚሰሩት። መጀመሪያ በፍቅር ያጠምዳሉ፣ እንደሚለዩዋችሁ ያስፈራራሉ፣ ይዝታሉ፣ ገንዘብ ይጠይቃሉ። ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች ግንኙነትን ዘላቂ እንደሚያደርጉ ይታሳበል። አንዱ ለአንዱ ሲሸነፍ የእውነት ይመስላል። ዘዴዎቹ በስሌት ነው የሚከናወኑት። ስሌቶቹ ደግሞ ይሰራሉ” ሲሉ የተጠኑ አካሄዶችን እንደሚጠቀሙ ያስረዳሉ።
“እንደ ሰው አንዳችን ሌላኛችንን ለመርዳት የተሳሰርን ነን። እንደዚያ ነው የተሰራነው” ይላሉ።
ቫኔሳ ይህን ጭካኔ የተሞላበት የማጭበርበር ስልት እንደምትጠላው ትናገራለች። “ፍቅር ያሳዩና ይጠፋሉ። ከዚያም ወንዶቹ ያጡትን ለመመለስ ምንም ነገር ለማድረግ ፈቃደኛ ይሆናሉ” ትላለች።
ዶ/ር ሬጊ፣ ሮቤርቶ የተጭበረበረው በተደራጀ ቡድን እንደሆነ ያስባሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት በቱርክ፣ በቻይና፣ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በናይጄሪያ እና በጋና በርካታ ቁጥር ያላቸው አባላት ያሏቸው በዓለም ላይ የሚሰሩ ትላልቅ የማጭበርበር ኔትዎርኮች አሉ።
ሮቤርቶ ገንዘብ እንዲልክ የተጠየቀበት ቦታ ጋና ነው።
ጋና ‘ሳካዋ ቦይስ’ የተባለ የኦንላይን አጭበርባሪዎች መናኸሪያ ነች።
ቢቢሲ የተወሰኑትን ለመከታተል ሞክሮ ነበር።
የጋናው ‘ሳካዋ ቦይስ’
ኦፋ የተባለ አንድ ወጣት ሰዎችን ለማጥመድ እና ትኩረት ለመሳብ ጊዜ እንደሚወስድ እንዲሁም የሐሰት መረጃዎችን ለመከታተል ብቻ ብዙ ጥረትን የሚጠይቅ እንደሆነ ይናገራል።
ይህ ወጣት “ሥራው መጥፎ ስሜት እንዲሰማኝ አድርጎኛል” ይላል። ይሁን እንጂ በዚህ ሥራ እስካሁን 50 ሺህ ዶላር እንዳገኘ አምኗል።
ኦፋ እንደሚለው የጃኔሳን ፎቶ ሲመለከት እርሱ እራሱ ባይጠቀምበትም፤ ነገር ግን በአጭበርባሪዎች ዘንድ ተወዳጅ እንደሚሆን ተረድቶ ነበር።
በተጨማሪም የማጭበርበሩ ሥራ እውነተኛ እንዲመስልለት ምስላቸውን የሚጠቀማቸውን ሴቶች የዕለት ተዕለት ሁኔታዎች ማለትም፣ ምግብ ሲሰሩ፣ ጂምናዚየም ውስጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እና መሰል ፎቶዎች እንደሚያስፈልጉ ያስረዳል።
ቫኔሳ የእርሷም ፎቶዎች በተወሰነ መልኩ ጥቅም ላይ እንደዋሉ ታስባለች።
“ምክንያቱም የዕለት ተዕለት ሕይወቴን የሚያሳዩ ፎቶዎችን ስለማጋራ ሙሉ ራሴን አጋልጬ ሰጥቻለሁ። በእነርሱ ለመጠቀም ብዙ አማራጭ ነበራቸው” ብላለች።
ነገር ግን በእርሷ ሙያዊ ማንነት እና እውነተኛ ማንነቷ መካከል ግልጽ የሆነ መስመር አስምራለች። ቫኔሳ ጭንቀት አለባት። ጃኔሳ ግን የለባትም።
ማብቂያ የሌለው የተጎጂዎች ቅሬታ ቫኔሳን እያሳዘነ ነው።
ካሜራ ላይ ትዕይንት ማቅረብ የአዕምሮ ጤናዋን እና ትዳሯን መጉዳት ጀምሯል።
በዚህ የተሰላቸችው ቫኔሳ፣ ከፕሮግራሟ ቀደም ብላ መጠጣት መጀመሯን ትናገራለች። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የራሷን ደስታ ማጣት ስለምታይበት ቪዲዮዎችን ማየት ትጠላለች።
እአአ በ2016 ከዚህ በላይ መሄድ እንደማትችል ስላመነች ሥራዋን ለማቆም ወሰነች።
መኪናዋን ይዛ፣ ቤቷን እና ትዳሯን ጥላ አዲስ ሕይወት ጀምራለች።
አሁን ቴራፒስት ሆና እያሰለጠነች እና የግል ማስታወሻዋን እየጻፈች ነው።
ቫኔሳ የእሷን ፎቶዎች ተጠቅመው ስላጭበርበሩት ሰዎች ሪፖርት ለማድረግ ወደ ባለሥልጣናት ሄዳ እንደማታውቅ ትናገራለች። ምክንያቱም ቅሬታዋን ትኩረት ሰጥተው ያዩታል ብላ አታስብም።
“ይመለከቱኝ እና ‘አንቺ የወሲብ ፊልም ኮከብ ነሽ?!’ ሲሉ ፊቴ ላይ ይሳለቃሉ” ብላለች።
ቫኔሳ አሁን ጠንካራ ሆናለች። አጭባርባሪዎች እርሷን ለመመስል መሞከራቸው መቼም የማይቀር መሆኑን ብታውቅም፣ አንዳንድ ሰዎች ለምን በእንዲህ ዓይነት ወጥመድ ውስጥ እንደሚገቡ ግን ተረድታለች።
“ሁላችንም በፍቅር ሲመጡብን ዲዳ እንሆናለን። እኔም እዚያ ውስጥ ነበርኩ። በሁላችንም ላይ የሚያጋጥም ነው” ብላለች ቫኔሳ።












