የቴክሳሷ ነዋሪ 'በሆዴ ያለችው ልጄ እንደ ተሳፋሪ ትቆጠር' በማለት እየተከራከረች ትገኛለች

የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ 50 ዓመታት በኋላ የጽንስ ማቐረጥን የሚከለክል ውሳኔ አሳልፏል
ታትሟል

በቴክሳስ የምትኖረዋ ብራንዲ ከ ሁለት ሰው በላይ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ብቻ የሚጠቀሙበት መንገድ ላይ በመገኘቷ የተጣለባትን ቅጣት ተከትሎ በሆዴ ያለችው ልጅ እንደ ሙሉ ሕጋዊ እና ባለመብት ሰው ትቆጠራለች ስትል እየተከራከረች ትገኛለች።

ከሳምንታት በፊት የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጽንስ ማቋረጥን አስመልክቶ የሰጠውን ውሳኔ ለክርክሯ መሰረት ማድረጓ ደግሞ አቐሟን ከተራ ክርክር ይልቅ ቀልብ የሚስብ የሕግ ሙግት ያደርገዋል።

 የ32 ዓመቷ ብራንዲ ቦቶን የስድስት አመት ልጇን ለማምጣት ቸኩላ ይህንን መንገድ እየተጠቀመች ባለችበት ወቅት ነው ፖሊስ የ275 ዶላር የቅጣት ደረሰኝ የቆረጠላት።

ይህንን ለመከራከርም የአሜሪካ የመጨረሻው የሕግ ውሳኔ ሰጪ አካል በ'ሮይ ቨርሰስ ዌድ' መካከል የተደረገውን ክርክር ላይ አሳልፎት የቆየውን የጽንስ ማቋረጥ መብት ከ50 ዓመታት በኋላ ለመሻር የሰጠው አዲስ ትንታኔ ለክርከሯ መሰረት ነው።

 ፍርድ ቤቱ ከ 15 ሳምንት በላይ የሆነውን ጽንስ ማቋረጥ ሕገ ወጥ ነው ሲል ወስኗል። ታዲያ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያልተወለደ ልጅ ሕጋዊ ሰውነት እና መብት አለው ብሎ ውሳኔ መስጠቱ ለክርክሬ መሰረት ነው ብላለች። ጉዳዩንም ወደ ፍርድ ቤት ይዛ ለመሄድ አስባለች።

ስትጓዝ የነበረችበትን መኪና ያስቆመው ፖሊስ ሌሎች ሰዎችን አሳፍራ እንደሆነ ሲጠይቃት ወደ ሆዷ እያመለከተች “ልጄ እዚህ ውስጥ አለች፣ እሷም ሕጋዊ ሰው ነች” ማለቷን ተናግራለች።

የፖሊስ መኮንኑ መንገዱ ሁለት ሰዎችን "ከሆድ ውጭ" መመልከት እንደሚያስፈልግ በመገለጽ ቅጣቱን እንደሰጣትም ተናግራለች።

የቴክሳስ ግዛት ከጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስቀድሞ ጽንስ ማቋረጥ ከከለከሉ 13 የአሜሪካ ግዛቶች መካከል አንዱ ነው።

 በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የቴክሳስ ፍርድ ቤት በግዛቱ ውስጥ ፅንስ የሚያቋርጡ ክሊኒኮች ለሁለት ሳምንታት አገልግሎታቸውን መስጠት እንዲችሉ ጊዜያዊ ትዕዛዝ ቢሰጥም ይህ ውሳኔ በቴክሳስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ታግዷል።

ታዲያ የዚህ ግዛት ነዋሪ የሆነችው ቦቶን ለዋሽንግተን ፖስት እንደተናገረችው "በፖሊሱ እንድቆም መጠየቄ እንግዳ ነገር ነው ብዬ ስላሰብኩ፣ ቴክሳስ ውስጥ እየሆነ ያለውን ነገር ከግምት ውስጥ በመክተት ይሄ እንደ ሕጻን ልጅ ይቆጠራል'' ስትልም ተናግራለች።

በተጨማሪም ቦቶን ከዚህ ቀደም እርጉዝ በነበረችበት ወቅት ብዙ ቁጥር ያለው ሰው የያዙ ተሽከርካሪዎችን የሚያስተናግውን ይህንን መንገድ ስትጠቀም መቆየቷን ትናገራለች።

 አክላም ሴቶች በአካላቸው ላይ ሙሉ መብት እና ምርጫ ሊኖራቸው እንደሚገባ እንደምታምን ለዋሽንግተን ፖስት የገለጸችው ግለሰቧ "ይህ ማለት ግን እኔም ብሆን የጽንስ ማቋረጥ መብት ደጋፊ ነኝ ማለት ግን አይደለም'' ብላለች።

ምንም እንኳን የቴክሳስ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ያልተወለደ ህጻንን እንደ ሕጋዊ ሰው እውቅና ቢሰጥም በግዛቱ ያሉ የትራንስፖርት ሕጎች ግን ይህንን አያሳዩም።

የሕግ ባለሙያዎች የቦቶን ጉዳይ ባለፈው ወር የጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ ያሉበትን ያልጠሩ ክፍሎችን የሚያንጸባርቅ ሲሉ ገልጸውታል።