በዩክሬን ደን ውስጥ በጅምላ የተቀበሩ የበርካታ ሰዎች አስክሬን ተገኘ

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች
ታትሟል

ዩክሬን ውስጥ በሚገኘውና ኢዚዮም ተብሎ በመታወቀው ደን ውስጥ በጅምላ ተቀብረው የነበሩ አስክሬኖች ተገኝተው እንዲወጡ እየተደረገ መሆኑ ተዘገበ።

የአገሪቱ ባለሥልጣናት በቦታው የጦር ወንጀል እንደተፈጸመ እንደሚያምኑ አመልክተው፣ ይህንንም ሰንደው ለማስቀመጥ እየሞከሩ መሆናቸው ተነግሯል።

ወደ 100 የሚጠጉ የዩክሬን የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በአካባቢው ባደረጉት ቁፋሮ በጊዜያዊ መቃብር በጅምላ የተቀበሩ ሰዎችን አስከሬን አግኝተዋል።

ይህ አካባቢ በቅርቡ በዩክሬን ኃይሎች ከሩሲያ ወታደሮች ይዞታ ነጻ የወጣ ሲሆን፣ በደኑ ውስጥ አስክሬናቸው የተገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በምን ምክንያት ሕይወታቸው እንዳለፈ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል።

ኢዚዮም የተባለው አካባቢ ባለፈው ግንቦት ወር በሩሲያ ኃይሎች ከተያዘ በኋላ የሠራዊቱ ዋነኛ ወታደራዊ መቀመጫ ሆኖ አገልግሏል።

ቁፋሮው በተካሄደበት ወቅት አንዳንድ ሠራተኞች በድንጋጤ እጃቸውን ራሳቸው ላይ ሲጭኑ፣ ሌሎች ደግሞ ከአካባቢው ገለል ሲሉ ታይተዋል።

የዩክሬን መንግሥት ዐቃቤ ሕግ ኦሌክሳንደር ሊየንኮቭ፣ በአካባቢው የጦር ወንጀል እንደተፈጸመ ይናገራሉ።

“በመጀመሪያው መቃብር አንድ ንጹህ ዜጋ አንገቱ ላይ ገመድ ታስሮ አግኝተናል። እንግልት ደርሶበት ነበር ማለት ነው። አብዛኞቹ የተገደሉት በሩሲያ ወታደሮች ነው። አንዳንዶቹ ተሰቃይተው ሲገደሉ በሩሲያ የአየር ጥቃት ሳቢያ የሞቱም አሉ” ብለዋል።

  በኢዚዮም ምን ተገኘ?

ዩክሬንን ይህንን አሰቃቂ የጅምላ መቃብር ለዓለም ማሳየትን መርጣለች።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በአካባቢው የተፈጸመውን እንዲመለከቱ ተጠርተዋል።

ከእንጨት የተሠራ መስቀል የተተከለባቸው መቃብሮችም በአካባቢው ይታያሉ። በአንዳንቹ ላይ የሰዎች ስም ተጽፏል። አብዛኞቹ ግን በቁጥር ነው የተለዩት።

በአካባቢው ሰዎች የተቀበሩት የሩሲያ ኃይሎች ተቆጣጥረውት በነበረ ወቅት ነው ተብሏል።

የዩክሬን ፖሊስ 445 መቃብሮች እንደተገኙ አስታውቋል።

አንዳንዶቹ መቃብሮች ከአንድ በላይ የሆኑ የሰዎች አስከሬን ይዘዋል።

አብዛኞቹ ንጹሀን ዜጎች ሲሆኑ፣ ሴቶችና ሕጻናትም ይገኙበታል ተብሏል።

ዐቃቤ ሕግ እንዳለው አንዳንዶቹ በሩሲያ የአየር ድብደባ የተገደሉ ናቸው።

ከዚህ ቀደም በአንድ የጋራ መኖሪያ ሕንጻ ላይ በደረሰ የአየር ጥቃት 47 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

ከመቃብሮቹ አንደኛው የ20 ወታደሮች አስክሬን እንደተገኘበትም ተገልጿል።

የተወሰኑት እጃቸው የፊጥኝ ታስሯል። አንደኛው አንገቱ ላይ ገመድ ተሸምቅቆበታል።

የፀጥታ ኃይሎች አስክሬኖቹን ለማውጥት መሬቱን በፈንጂ መክፈት ነበረባቸው።

ሂርዮሪ በአካባቢው ከፍተኛ የአየር ድብደባ በተደረገበት ወቅት ነበር ባለቤታቸው የተገደሉት
የምስሉ መግለጫ, ሂርዮሪ በአካባቢው ከፍተኛ የአየር ድብደባ በተደረገበት ወቅት ነበር ባለቤታቸው የተገደሉት

ባለቤታቸውን ቤታቸው ጀርባ የቀበሩት አዛውንት

ሂርዮሪ የ72 ዓመት አዛውንት ናቸው።

በአካባቢው ከፍተኛ የአየር ድብደባ በተደረገበት ወቅት ነበር ባለቤታቸው የተገደሉት።

ከዚያም ባለቤታቸው ሉድሚላን ቤታቸው ጀርባ ቀብረዋቸዋል።

ብዙም ሳይቆዩ ደግሞ ባለቤታቸውን በኢዚዮም ዳግመኛ ቀብረዋል።

ኢዚዮም ደን አሁን እየተቆፈረ ስለሆነ ባለቤታቸው ለሦስተኛ ጊዜ አስክሬናቸው ይወጣል።

ዩክሬን በአካባቢው ዝርዝር ምርመራ ማድረግ የጀመረችው የሩሲያ ኃይሎች ከአካባቢው መውጣታቸውን ተከትሎ ነው።

ከዚህ ደን አቅራቢያ የምትኖር ግለሰብ እንደተናገረችው፣ የሩሲያ ወታደሮች ማንንም ወደ ደኑ አያስጠጉም ነበር።

ማክሲም የተባለ የአካባቢው ነዋሪ በመቃብር ስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች የደረሰበትን ስቃይ ሲናገር ነበር።

ከሳምንታት በፊት በሩሲያ ኃይሎች ታግቶ ቆይቶ፣ የዩክሬን ኃይሎች አካባቢው ሲቆጣጠሩ ነበር ነጻ የወጣው።

እጁ ታስሮ የቆየበትን ጠባሳ ያሳየው ማክሲም፣ በኤሌክትሪክ ገመድ እንደተሰቃየም ተናግሯል።

“የተፈጸመውን እናወግዛለን”

የፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ከፍተኛ አማካሪ ሚካሄሎ ፖዶሊክ እንደተናገሩት፣ አስክሬናቸው ከተገኙ ሰዎች መካከል ማሰቃየት የተፈጸመባቸው እንዳሉ ታውቋል።

“በአካባቢው ጨለማ ውስጥ ያለ ምግብ እና ውሃ እንዲቆዩ የተደረጉ ሰዎች አግኝተናል። ፍትሕም አላገኙም” ብለዋል።

የዩክሬን ዐቃቤ ሕግ እንዳሉት፣ በቅርቡ በዩክሬን ኃይሎች በተያዙ ሌሎች አካባቢዎችን የመቃብር ስፍራዎች ተገኝተዋል።

የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፣ በኢዚዮም ደን መቃብሮች መገኘታቸው “እጅግ አስደንጋጭ ነው” ብለዋል።

አያይዘውም “አስደንጋጭ ቢሆንም የሩሲያ ኃይሎች ዩክሬን ውስጥ ከፈጸሟቸው ጭካኔ የተሞሉ ወንጀሎች ጋር የሚመሳሰል” ሲሉ አክለዋል።

አሜሪካ የጦር ወንጀል በመሰነድ ድጋፍ መስጠት እንደምትቀጥል ተናግረዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “የተፈጸመውን እጅግ እናወግዛለን” ብለዋል።

ዓለም አቀፍ ወንጀሎችን በመመርመር የሚታወቁት የዩናይትድ ኪንግደሙ ጠበቃ ናይጅል ፖቮዋን እንዳሉት፣ በአካባቢው የተቀበሩ አስክሬኖች ሲወጡ የጦር ወንጀል ስለመፈጸሙ ማስረጃ ሊገኝ ይችላል።

“የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት በጣም ገና ቢሆንም ምልክቶቹ አሉ። አንዳንዶቹ ሰዎች በአየር ድብደባ ሲሞቱ፣ ምግብ ባለማግኘትና ሕክምና በማጣት የሞቱም ጥቂት አይደሉም” ብለዋል።

ጨምረውም “የሰዎቹ አስክሬን ከወጣ በኋላ እንግልት እንደደረሰባቸው የሚጠቁሙ መረጃች እንደሚገኙ አልጠራጠርም። በሌሎች በሩሲያ ተይዘው በነበሩ አካባቢዎች የተገኙት ማስረጃዎችን እንደ ማሳያ መውሰድ እንችላለን” ሲሉ አክለዋል።