በቻይና በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለ በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ተመዘገበ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ቻይና ምንም እንኳን የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል አሁንም ጥብቅ ቁጥጥር ላይ ብትሆንም ወረርሽኙ ከጀመረ አንስቶ በአንድ ቀን ከፍተኛ የተባለውን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መዘገበች።
ዋና መዲናዋን ቤይጂንግን እና ደቡባዊ የንግድ ማዕከሏን ጉዋንዡን ጨምሮ በበርካታ ከተሞችም ወረርሽኙ እንደገና አገርሽቷል።
ረቡዕ ዕለት አገሪቷ 31 ሺህ 527 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን፣ ይህም ሚያዝያ ላይ ወረርሽኙ በከፋበት እና በትልቋ ከተማ ሻንጋይ የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለበት ወቅት ከፍተኛ ተብሎ ከተመዘገበው የሚበልጥ ነው።
በዚያን ወቅት በአንድ ቀን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከፍተኛው ቁጥር 28 ሺህ ነበር።
አሁን ላይ ወረርሸኙ በመላ አገሪቱ ማገርሸቱ የተሰማው የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የተጣለው ጥብቅ የእንቅስቃሰሴ ገደብ መቀጠሉን ተከትሎ በተከታታይ ተቃውሞ በተከሰተበት ወቅት ነው።
የቻይና ዜሮ ኮቪድ ፖሊስ 1.4 ቢሊየን ሕዝብ ባላት አገር የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ያተረፈ ቢሆንም በኢኮኖሚው እና በነዋሪው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ የተሰማውም አገሪቷ በመጠኑም ቢሆን የጣለችውን ጥብቅ ገደቦችን ካላላች ከሳምንታት በኋላ ነው።
ባለዘበችው በዚህ ሕጓ በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ንክኪ ያለው ሰው በመንግሥት ለይቶ ማቆያ ስፍራ ለሰባት ቀናት እንዲቆይ የሚለውን ወደ አምስት ዝቅ ያደረገች ሲሆን፣ ተጨማሪ ሦስት ቀናት በቤት ውስጥ ራሳቸውን እንዲያገሉ አድርጋ ነበር።
ከዚህም ባሻገርም በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር በቀጥታ ንክኪ ካለው ሰው ጋር ግንኙነት ያለውን ሁለተኛ ሰው መመዝገብ አቁማለች። ይህም በርካታ ሰዎች ለይቶ ማቆያ እንዳይገቡ አድርጓል።
ባለሥልጣናት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይም በሻንግሃይ ላይ የተጣለውን ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ለማንሳት እያሰቡ ነበር ።
ይሁን እንጂ በቤይጂንግ በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመርንና በወራት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተውን የኮቪድ 19 ሞት ተጋፍጠዋል። በመሆኑም ባለሥልጣናት የተወሰኑ ገደቦችን አሁንም በበርካታ አካባቢዎች ፣ ሱቆች፣ ትምህርት ቤቶች እና ምግብ ቤቶች እየተገበሩ ነው።
ስድስት ሚሊየን ነዋሪዎች ባሏት ማዕከላዊ ከተማዋ ዣንግዡ ከአርብ ዕለት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የእንቅስቃሴ ገደብ እንደሚጣልም ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ይህም የተነገረው ባለቤትነቱ የአይፎን አምራቹ ፎክስኮን በሆነው ግዙፍ ኩባንያ ላይ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ነው። ኩባንያው በክፍያ ሥርዓቱ ላይ ስላጋጠመው "ቴክኒካዊ ስህተት" ይቅርታ ጠይቋል።
ባለፈው ሳምንት ዣንግዡ አንድ ሕጻን በኮቪድ ገደቦች ምክንያት በአፋጣኝ የህክምና አገልግሎት ሳያገኝ ሕይወቱ በማለፉ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሶ ነበር።
ቻይና አሁንም ሰፊ ምርምራ በማካሄድና የእንቅስቃሴ ገደብ በመጣል ከኮቪድ ወረርሽኝ ለመላቀቅ እየታገለች ያለች የመጨረሻዋ አገር ናት።
ሆኖም አሁን ላይ በመላ አገሪቷ 31 ግዛቶች ውስጥ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ተመዝግበዋል።
ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በአገሪቷ ከፍተኛ ቁጥር የሚዙትን በእድሜ የገፉ ሰዎችን ለመጠበቅ ጥብቅ ገደብ መጣል ያስፈልጋል ብለዋል።
ከሌሎች ያደጉ አገራት ጋር ሲነጻጸርም በቻይና የተከተቡ ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ክትባት ያገኙት ግማሽ ያህሉ ከ80 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎቿ ብቻ ናቸው።
በቻይና በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ በሆንም ቁጥሩ ግን ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ በደረሰበት ወቅት ከፍተኛ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከተመዘገበባቸው አገራት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ያነሰ ነው።
በቻይና ወረርሽኙ ከተከሰተ አንስቶ ከ5 ሺህ 200 በላይ ሰዎች መሞታቸው በይፋ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጻር ዝቅተኛ ነው።
ይህ ማለት በቻይና ከአንድ ሚለየን ሕዝብ ሦስት ሞቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በአሜሪካ ከ1 ሚሊየን ሕዝብ 3 ሺህ፣ በዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ 2 ሺህ አራት መቶ ሰዎች ሞተዋል ማለት ነው።












