ቻይና በአሜሪካ ምድር ፖሊስ ጣቢያዎች አሏት መባሉ ኤፍቢአይን አሳስቦታል  

የቻይና ሰንደቅ ዓላማ በኒው ዮርክ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ከቻይና ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ሚስጥራዊ "ፖሊስ ጣቢያዎች" በመላው ዩናይትድ ስቴትስ መቋቋማቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች መውጣታቸው ኤፍቢአይን አሳስቦታል።

ሴፍጋርድ ዲፌንደርስ በተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የወጣው ሪፖርት እንደሚያትተው ኒው ዮርክን ጨምሮ በመላው ዓለም ፖሊስ ጣቢያዎቹ መኖራቸውን አጋልጧል።

የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሪስቶፈር ሬይ ለከፍተኛ ፖለቲከኞች እንደተናገሩት ኤጀንሲው በመላው ሃገሪቱ እነዚህ ፖሊስ ጣቢያዎች ስለመኖራቸው እየተከታተለ ነው።

"እነዚህ ጣቢያዎች መኖራቸውን እናውቃለን" ብለዋል ሬይ።

“ቻይና ፖሊስ ጣቢያ ለማቋቋም ትሞክራለች ብሎ ማሰብ በራሱ አሳፋሪ ነገር ነው። ሉዓላዊነትን ከመጣስ ባለፈ የዳኝነት እና የሕግ ማስከበር የትብብር ሂደቶችንም ያቋርጣል" ብለዋል።

ጣቢያዎቹ የአሜሪካን ህግ ይጥሳሉ ወይ ተብለው ሲጠየቁም ኤፍቢአይ "ህጋዊ ጉዳዮችን እየተመለከተ ነው" ሲሉ መልሰዋል።

ኃላፊው ይህን የተናገሩት ለዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት የሃገር ውስጥ ደህንነት እና የመንግሥት ጉዳዮች ኮሚቴ ላይ በከፍተኛ የህግ አውጭዎችም ጥያቄዎች ተሰንዝሮላቸዋል።

መቀመጫውን በስፔን ያደረገው መንግሥታዊ ያልሆነው ሴፍጋርድ ዲፌንደርስ እንዳለው የቻይና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ በተለያዩ አህጉራት “የውጭ የፖሊስ አገልግሎት ጣቢያዎችን” አቋቁሟል። ሁለቱን በለንደን ሲሆኑ አንዱ በግላስጎው ነው። በሰሜን አሜሪካ ደግሞ ጣቢያዎቹ በቶሮንቶ እና በኒው ዮርክ ይገኛሉ።

ጣቢያዎቹ የተቋቋሙት ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከል እና በውጭ ላሉ ቻይናውያን እንደ መንጃ ፍቃድ ማደስ እና ሌሎች የቆንስላ አገልግሎቶችን የመሰሉ አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት ነው ተብሏል።

ሴፌጋርድ አክሎም “ከባህር ማዶ ቻይናውያን ጋር የተያያዙ ሁሉንም አይነት ህገወጥ እና የወንጀል ድርጊቶችን ለመከላከልም” እንደሚያገለግሉ ገልጿል።

ቻይናያ እነዚህን የፖሊስ ጣቢያዎችን ስለማቋቋሟ አስተባብላለች።

ሬይ እንዳሉት የቻይናውን ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ላይ የተቃወሙትን ሰዎች ከማዋከብ፣ ከማሳደድ፣ ከመከታተል እና ከማሸማቀቅ ጋር በተገናኘ የአሜሪካ መንግስት በርካታ ክሶችን ከፍቷል።

ዩናይትድ ስቴትስ በጥቅምት ወር የቻይና መንግሥት አንዱን ዜጋዋን ወደ ቻይና ለመመለስ ባደረገችው ጥረት በመሳተፍ አንድን የአሜሪካ ነዋሪ እና ቤተሰቡን በመሰለልና በማዋከብ በተከሰሱ ሰባት የቻይና ዜጎች ላይ ክስ ተመስርቷል።

በሴፍጋርድ ሪፖርት ምክንያት በአይሪሽ ዋና ከተማ ደብሊን ከሚገኙት የቻይና "ፖሊስ ጣቢያዎች" አንዱ እንዲዘጋ ባለፈው ወር በመንግሥት ታዝዟል።

የካናዳ የስለላ ባለስልጣናት በበኩላቸው ቻይና ይፋዊ ያልሆኑ "ፖሊስ" ጣቢያዎችን በካናዳ ምድር ከፍታለች የሚለውን ውንጀላ እየመረመሩ መሆኑን በቅርቡ ተናግረዋል።