ጠፍቶ የነበረው የአሜሪካ የጦር ጄት ስብርባሪ ተገኘ

የፎቶው ባለመብት, PA MEDIA
በአሜሪካዋ ግዛት ደቡብ ካሮላይና እየበረረ በነበረበት ወቅት አብራሪው በፓራሹት ከወረደ በኋላ ጠፍቶ የነበረው ኤፍ-35 የጦር ጄት ስብርባሪ መገኘቱን የጦር ባለሥልጣናት አስታወቁ።
እሑድ ከሰዓት በኋላ የጠፋውና 100 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣው የጦር አውሮፕላን ስብርባሪ በገጠራማዋ ዊሊያምስበርግ ካውንቲ መገኘቱን ባለስልጣናት ተናግረዋል።
ከአውሮፕላኑ ውስጥ በፓራሹት የወረደው አብራሪ ሆስፒታል ውስጥ በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።
የጦር ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ የጦር አውሮፕላኑ ስብርባሪ በሰሜን ቻርለስተን ከሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር፣ ጆይንት ቤዝ ቻርለስተን፣ ሰሜን ምስራቅ ሁለት ሰዓት በሚርቅ ቦታ መገኘቱን ገልጸዋል።
የጦሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተገኘው ስብርባሪ የጠፋው ጄት አካል መሆኑም ተረጋግጧል።
ሰኞ ዕለት ፍለጋው ከተጠናቀቀ በኋላም ጦሩ፣ ስላጋጠመው አደጋ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ገልጾ፣ የምርመራው ሂደት ላይ ተፅዕኖ ላለማሳደር ዝርዝር መረጃ መስጠት ከመስጠት ተቆጥቧል።
መርማሪዎች ሥራቸውን እንዲሰሩ ለማስቻልም ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲርቁም ተጠይቋል።
የጦር አውሮፕላኑ ከተሰወረ በኋላ የፌደራል አቪዬሽን የፍለጋ ቡድኖች አውሮፕላኑ ለመጨረሻ ጊዜ የታየበትን አካባቢ መሠረት በማድረግ ከቻርለስተን ከተማ በስተሰሜን በሞልቲር እና ማሪዮን ሐይቆች አካባቢ ፍለጋ ሲያካሂዱ ነበር።
ጆይንት ቤዝ ቻርለስተን በኤክስ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ አውሮፕላኑን ለመፈለግ የሕዝብ እርዳታን ጠይቆ ነበር።
ይህም በማኅበራዊ ሚዲያ እና በሕግ አውጭዎች ዘንድ መሳለቂያ ሆኖ ነበር።
የጦሩ ቃል አቀባይ ለኤንቢሲ እንደተናገሩት ከተዋጊ ጄቱ ውስጥ አብራሪው ሲወጣ ጄቱ ያለ አብራሪ እንዲበር ተደርጎ ወይም (አውቶፓይለት ሞድ) ላይ ተትቶ ነበር።
በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ እየበረረ ቆይቶ ሊሆን ስለሚችል ፍለጋውን ውስብስብ እንዳደረገው ጨምረው ተናግረዋል።
የመከላከያ አማካሪ ድርጅቱ ቲል ግሩፕ ከፍተኛ ተንታኝ የሆኑት ጄጄ ገርትለር ፣“ አብራሪው ሲወጣ የራዲዮ ሲግናል የሚቀበለው መሣሪያ በመቃጠሉ ጄቱ ያለበትን ትክክለኛውን ቦታ ለመከታተል አዳጋች ሆኖ ነበር” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ኤፍቢ-35 ቢ የጦር አውሮፕላን ንብረትነቱ ማሪን የተዋጊ ማሰልጠኛ ተቋም ክፍል 501 ሲሆን አብራሪዎችን ለማሰልጠን ጥቅም ላይ የሚውል የጦር አውሮፕላን ነው።
ሰኞ ዕለት የባሕር ኃይልንና እግረኛ ወታደሮችን የያዘው የአሜሪካ ጦር በዚህ ሳምንት በሁሉም ቅርንጫፎቹ የሚደረጉ የአየር ኦፕሬሽኖች ለሁለት ቀናት እንደሚቆሙ አስታውቋል።
ባለስልጣናትም በዚህ ሳምንት ውስጥ የአየር ጉዞ አደጋዎችና ክስተቶችን እንዲሁም ጥሩ ልምዶችን በተመለከተ ለመወያየት ማቀዳቸውን ጦሩ ጨምሮ ገልጿል።
የአሜሪካ ጦር ባለፉት 6 ሳምንታት ከ2.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ በሚያስከትል የአደጋ አይነት፣ አደጋ ሲያጋጥመው ይህ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑን ገልጿል። ሆኖም ከዚህ ቀደም ስላጋጠሙ አደጋዎች አላብራራም።
ነሐሴ ወር ላይ ሦስት ወታደሮች በጦር አውሮፕላን በደረሰ አደጋ የሞቱ ሲሆን ሌላ ወታደር ደግሞ በሳንዲያጎ አቅራቢያ ልምምድ ሲያደርግ ጄቱ በመከስከሱ ሕይወቱ አልፏል።
እንደ አውሮፓውያኑ 2018 የአሜሪካ ጦር በደቡብ ካሮላይና ግዛት ባጋጠመ የመከስከስ አደጋ ኤፍ-35 ጄቶችን በጊዜያዊነት ከበረራ አግዶ እንደነበርም ይታወሳል።












