ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ አየር ማረፊያዎች የተያዙ ሽጉጦች ቁጥር ታይቶ የማይታወቅ መሆኑ ተገለጸ
በአሜሪካ አየር ማረፊያዎች ከመንገደኞች ላይ በፍተሻ የተያዙ የጦር መሳሪያዎች ቁጥር ታይቶ የማይታወቅ መሆኑ ተገለጸ።
እስከ ታህሳስ ድረስ በአጠቃላይ 6 ሺህ 301 የጦር መሳሪያዎች ከመንገደኞች በፍተሻ የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 88 በመቶው ቀለሃዎችን በውስጦቻቸው እንደያዙ መሆኑ ተገልጿል።
የትራንስፖርት ደህንነት አስተዳደር በአውሮፓውያኑ ዓመት መጨረሻ ወደ 6 ሺህ 600 ሽጉጦች ሊደርስ እንደሚችል አስታውቋል።
ይህም አኃዝ በአውሮፓውያኑ 2021 ከነበረው 10 በመቶ ጭማሬ እንዳሳየ ጠቁሟል።
ወደ አየር ማረፊያዎቹ የሚገቡ ሽጉጦችን ለመቆጣጠርና ለመያዝ ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚባክንና ለተሳፋሪዎችም ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስወጣቸው ኤጀንሲው ገልጿል።
በባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት 5 ሺህ 972 የጦር መሳሪያዎች ተይዘው ነበር።
በአትላንታ፣ ጆርጂያ የሚገኘው ሃርትስፊልድ ጃክሰን አውሮፕላን ማረፊያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የጦር መሳሪያ በመያዝ የአንደኛነቱን ስፍራ ሲይዝ በቴክሳስ ግዛት የዳላስ ፎርት ዎርዝ አውሮፕላን ማረፊያ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ነበር።
መንገደኞች የጦር መሳሪያ ታጥቀው የአውሮፕላን ማረፊያ ጸጥታና ደህንነት ፍተሻዎችን ለማለፍ እንደሚሞክሩ አልተገለጸም።
የጦር መሳሪያ ይዞታን በተመለከተ የአሜሪካ ግዛቶች የተለያየ ህግጋት አላቸው። ነገር ግን ሰዎች ጦር መሳሪያ የመያዝ ፍቃድ ቢኖራቸውም በአውሮፕላኑ ውስጥ ታጥቀው መግባትን አይፈቅዱም።
የትራንስፖርት ደህንነት ባለስልጣናት በአውሮፕላን ማረፊያ ፍተሻ ጣቢያዎች ላይ መሳሪያ ካገኙ ሽጉጡ መቀባበል አለመቀባበሉን ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተለያየ የፍትሐ ብሄር ቅጣት ይጥላሉ።
ኤጀንሲው በአውሮፕላን ማረፊያ ፍተሻ ጣቢያዎች ላይ የጦር መሳሪያ ለሚይዙ ሰዎች ከፍተኛውን የፍትሐ ብሔር ቅጣት ከ13 ሺህ 910 ዶላር ወደ 14 ሺህ 950 ከፍ ሊያደርገው መሆኑንም ገልጿል።
መንገደኞች መሳሪያዎቻቸው አለመቀባበሉን አረጋግጠው በጠንካራና በተቆለፈ መያዣ ውስጥ አድርገው በአውሮፕላን ውስጥ መጓዝ ይችላሉ። ሆኖም መንገደኞች የጦር መሳሪያ ይዘው እንደሚጓዙ ቀድመው ለአየር መንገድ ተወካዮች ማሳወቅ አለባቸው።