በእስራኤል ቴላቪቭ በተቃጣ የሽብር ጥቃት አንድ ቱሪስት ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትናንት በእሰራኤል መዲና ቴላቪቭ አንድ አሸባሪ መኪና በማሽከርከር ሆን ብሎ ነዋሪዎችን በመግጨት ባደረሰው ጥቃት አንድ ጣሊያናዊ ሲገደል ሌሎች ስምንት ሰዎች ቆስለዋል።
ሟቹ ጣሊያናዊ አሌሳንድሮ ፓሪኒ የሚባል ሲሆን የቆሰሉት ስምንቱም ሰዎች በሙሉ ቱሪስቶች እንደሆኑ ታውቋል።
በጥቃት አድራሹ ይሽከረከር የነበረው መኪና ከጎዳና ወጥቶ እግረኞች በሚንቀሳቀሱበት ሰፊ ሜዳ ላይ ነው ሰዎችን ለመግጨት እየተንደረደረ የመጣው።
ከአደጋው በኋላ የወጡ ምሥሎች አንድ ነጭ የቤት መኪና ተገልብጦና ተጨራምቶ ቆሞ የሚያሳዩ ናቸው።
ፖሊስ ጥቃት አድራሹን ተኩሶ መግደሉን አስታውቋል።
ይህ ጥቃት የመጣው ዐርብ ዕለት የብሪታኒያ-እስራኤል ዝግነት ያላቸው ሁለት እህትማማቾች በኃይል በተያዘው የዌስት ባንክ አካባቢ ከተገደሉ በኋላ የደረሰ ሁለትኛ ጥቃት ነው።
በዚህ ዌስትባንክ በደረሰው ጥቃት የእህትማማቾቹ እናት ቆስለው በሕይወት ተርፈዋል።
ይህን የትናንት ምሽቱን ግጭት ያደረሰው ተጠርጣሪ የ45 ዓመት ጎልማሳ መሆኑን፣ ጥቃት ያደረሰበት መኪና ኪያ ሞዴል እንደሆነና ጥቃቱን ያደረሰው ደግሞ በባሕር ዳርቻ አቅራቢያ በሚገኝ የእግረኞች መዝናኛ ቦታ መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል።
ጥቃቱ ሲደርስ በቅርብ በሚገኝ ነዳጅ ማደያ የነበረ አንድ ፖሊስ ወደ ስፍራው ፈጥኖ በመድረስ ጥቃት አድራሹ መሣሪያ የሚመስል ነገር ይዞ ከመኪናው ሊወጣ ሲል ተኩሶ ገድሎታል ብሏል መግለጫው።
የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂዯርጂያ ሜሎኒ በጥቃቱ ማዘናቸውን፣ በዜጋቸው መሞት ልባቸው መሰበሩን ካወሱ በኋላ ጥቃቱን ‘የፈሪ ዱላ’ ሲሉ ጠርተውታል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ጥቃቱን ተከትሎ ስፍራውን ከጎበኙ በኋላ ፖሊስን ጨምሮ ተጠባባቂ ኃይል ጥበቃ እንዲያጠናክር አዘዋል።
ይህ ጥቃት የደረሰው የእስራኤል መከላከያ በሐማስ ላይ የአየር ጥቃት ካደረሰ ከሰዓታት በኋላ ነው።
ሐሙስ ዕለት ከሊባኖስ 34 ሮኬቶች ወደ እስራኤል የድንበር ከተማ ተወንጭፈው ሕንጻዎች ላይ መጠነኛ ጉዳት ካደረሱ በኋላ እስራኤል በምላሹ ከባድ የአየር ድብደባ በሐማስ ቁልፍ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ሰንዝራለች።
ከሰሞኑ በእስራኤልና ፍልስጤሞች መካከል ያገረሸው አለመግባባት መነሻ የሆነው የእስራኤል ፖሊስ በዚህ ሳምንት መጀመርያ አል አቅሳ መስጊድን ቅጥር ገብቶ ወረራና ፍተሻ በማድረጉ ነው።
ይህ ድርጊት ፍልስጤምን ጨምሮ የአካባቢው አገራትን አስቆጥቶ ነበር።
በሐማስ ከሊባኖስ የተተኮሱት ሮኬቶች ብዛት በ17 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ነው ተብሏል።
ሮኬቶቹ ሲወነጨፉ በሊባኖስ ጉብኝት ላይ የነበሩት የሐማስ መሪ ኢስማኤል ሐኒያ ‘ወራሪዋ እስራኤል ጥቃት ስታደርስብን መቼስ እጃችንን አጣጥፈን ቁጭ አንልም” ሲሉ ተናግረዋል።












