በኮንጎ የጣልያንን አምባሳደር ገድለዋል የተባሉ የዕድሜ ልክ እስራት ተበየነባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘው ወታደራዊ ፍርድ ቤት የጣልያንን አምባሳደርን ገድለዋል ባላቸው ስድስት ግለሰቦች ላይ የዕድሜ ልክ እስራት በይኖባቸዋል።
አምባሳደሩ የተገደሉት በአውሮፓውያኑ 2021 ነው።
ሉካ አታናሲዮ ሲጓዙ የነበረበት የተባበሩት መንግሥታት መኪና በደፈጣ ጥቃት ከደረሰበት በኋላ ከተገደሉ ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ ናቸው።
መኪናውን ሲያሽከረክር የነበረው የአምባሳደሩ ሹፌር ወዲያውኑ የተገደለ ሲሆን ጠባቂያቸውም ታግቶ ነበር። ሆኖም ጠባቂያቸውን ከታጋቾች ለማስመለጥ በነበረው ዘመቻ ስህተት በመሰራቱ ህይወቱ አልፏል።
ክስተቱ የተፈጸመው የታጠቁ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱበት በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ውስጥ ነው።
አምባሳደሩ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ምገባ ፕሮግራም ለመጎብኘት የየኑኔስኮ የዓለም ቅርስ ስፍራ በሆነው ቪሩንጋ ብሔራዊ ፓርክ በኩል እየተጓዙ እያለም ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተገልጿል።
አምባሳደሩን በመግደል ከተከሰሱት ስድስት ሰዎች መካከል አምስቱ ባለፈው ዓመት ጥር ላይ በቁጥጥር ስር ውለው በመዲናዋ ኬንሻሳ በሚገኘው በንዶሎ ወታደራዊ እስር ቤት ይገኛሉ። ስድስተኛው ተጠርጣሪ በሽሽት ላይ ነው ተብሏል።
ተከሳሾቹ አሽከርካሪውን ሙስጠፋ ሚላምቦን ከገደሉ በኋላ አምባሳደሩን እና ጠባቂያቸውን ቪቶሪዮ ኢኮቫቺን በማገት ካሳ ለመጠየቅ አስቦ የነበረ “ወንጀለኛ ቡድን” አካል መሆናቸውን አቃቤ ህግ አስታውቋል።
አቃቤ ህግ ጎዴ ባሙሳምባ ካባምባ ግለሰቦቹ በሞት ቅጣት እንዲቀጡም ጠይቀዋል።
ችሎቱ ጥቅምት ወር የጀመረ ሲሆን ተከሳሾቹ የእምነት ክህደት ቃላቸውን በሚሰጡበትም ወቅት ያሰቃይዋቸው እንደነበር ተናግረዋል።
የተከሳቹ ጠበቃ ጆሴፍ አምዛቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በእድሜ ልክ እስራት ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ነው።
ችሎቱ ፍትሃዊ እንዳልሆነ የገለጹት ጠበቃው ከጥቃቱ የተረፉ አራት ግለሰቦች አንዳቸውም ለምስክርነት በችሎት ላይ አለመቅረባቸውንም ጠቅሰዋል።
እንደ ጠበቃቸው ገለጸ ሁሉም ተጠርጣሪዎች በሞተር ሳይክል ሹፌርነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ ሲሆን ለተጎጂ ቤተሰቦች 2 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ ተወስኗል።












