በደቡብ አፍሪካ ስደተኞች እንዲወጡ የተቀመጠው ቀነ ገደብ መቃረቡን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዜጎች እንዲጠነቀቁ አሳሰበ

የደቡብ አፍሪካ ፀረ ስደተኞች ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የደቡብ አፍሪካ ፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ መሪዎች ስደተኞች ከአገሪቱ እንዲወጡ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ መቃረቡን ተከትሎ፤ በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች "ጥንቃቄ" እንዲያደርጉ አሳሰበ።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ስደተኞች እስከሚቀጥለው ሳምንት ማክሰኞ ሰኔ 23/2018 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ በፀረ ስደተኞች እንቅስቃሴ መሪዎች ቀነ ገደብ መቀመጡ ይታወሳል።

በሕገ ወጥ ስደተኞች ላይ እንደሚሠራ የሚገልጸው 'ማርች ኤንድ ማርች' የተሰኘው እንቅስቃሴ መሪ ጃሲንታ እንጎቤሴ ዙማ በሰጡት መግለጫ ይህ ቀነ ገደብ እንደተጠበቀ መሆኑን ተናግረዋል።

በፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ትናንት ሐሙስ ሰኔ 18 ቀን ባወጣው ማሳሰቢያ፤ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሁኔታን አስመልክቶ "ከመንግሥት ጋር አስፈላጊውን ግንኙነት" እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት "ስደተኞች ላይ የኃይል ጥቃት" እንዳይደርስ ጥበቃ እንደሚያደርግ ሲገልጽ መቆየቱን አስታውሶም፤ የአገሪቱ መንግሥት "በቀጣይ ቀናት የፀጥታ ማስከበር ተግባሩን እንደሚያጠናክር ይጠበቃል" ብሏል።

ይሁን እንጂ ስደተኞች ላይ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ያለውን ስጋት ገልጿል። "በስደተኞች ላይ ሕገ ወጥ ድርጊት እና ጥቃቶች ሊፈጸሙ የሚችሉበት ሁኔታዎች እንዳሉ የሚጠቁሙ አዝማሚያዎች አሁንም ይስተዋላሉ" ሲል በመግለጫው አስፍሯል።

"የመብት መጣስ እና የደኅንነት ስጋቶች" መኖራቸውን የገለጸው ኤምባሲው፤ በዚህም የተነሳ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች "የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችሁን ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ እንድታደርጉ" ሲል ዜጎቹን አሳስቧል።

በየአካባቢያቸው ከሚገኙ የመንግሥት አካላት እና የኮሚዩኒቲ አደረጃጀቶች ጋር የቅርብ ግንኙነት እንዲያደርጉም መክሯል። ከእነዚህ አካላት ጋር "መረጃ በመለዋወጥ ከወዲሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ ኤምባሲው ማሳሰቢያ ያቀርባል" ሲልም አስጠንቅቋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኤምባሲው ከሁለት ወር በፊት በቀናት ልዩነት አራት ኢትዮጵያውያን መገደላቸው በተሰማበት ወቅት የአገሪቱ መንግሥት ግድያውን በተመለከተ "በአስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ" እና "ችግር በሚታይባቸው አካባቢዎች ልዩ ጥበቃ" እንዲያደርግ መጠየቁን አስታውቆ ነበር።

ኤምባሲው በወቅቱ ባወጣው መግለጫ ግድያዎቹ በደቡብ አፍሪካ ከሚታየው መጤ ጠልነት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችልም ገልጾ ነበር።

ከዚያ ጊዜ በኋላ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚካሄዱ የፀረ ስደተኞች ሰልፎች ተበራክተዋል። የተለያዩ አገራት ስደተኞች ላይ ጥቃት ሲፈጸም ያሳያሉ የተባሉ ቪዲዮዎችም ተሠራጭተዋል።

በእነዚህ እንቅስቃሴዎች የተነሳ ስደተኞች ላይ ስጋት በመፈጠሩ ናይጄሪያ እና ጋና ዜጎቻቸውን ከደቡብ አፍሪካ አስወጥተዋል።

የዚህ እንቅስቃሴ መሪዎች ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ከደቡብ አፍሪካ እንዲወጡ ቀነ ገደብ በተቀመጠበት ሰኔ 23 ቀን ሰልፍ እንዲካሄድ አስታውቀዋል።

"ማንም ሰው ላይ ጉዳት ማድረስም ዓላማችን አይደለም። እኛ የምንጠይቀው ነገር ቢኖር ሕገ-ወጥ ስደተኞች አገራችንን ለቅቀው እንዲወጡ እና መንግሥት ቀድሞውኑ ያሉትን ሕጎች እንዲያስከብር ብቻ ነው" ሲሉ የማርች ኤንድ ማርች መሪ ተናግረዋል።

ይህ ለስደተኞች የተቀመጠው ቀነ ገደብ በአፍሪካ ሕብረት ስር ከሚገኘው እና የዳኝነት አካል ከሆነው የአፍሪካ የሰብአዊ እና ሰዎች መብቶች ኮሚሽን ትችት ቀርቦበታል።

ኮሚሽኑ ትናንት ሐሙስ ባወጣው መግለጫ፤ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የተደራጁ ቡድኖች "በሌሎች የአፍሪካ አገራት ዜጎች ላይ" ያስቀመጡት ቀነ ገደብ "ጥልቅ ስጋት" እንደተሰማው ገልጿል።

መግለጫው፤ "ኮሚሽኑ ኦፕሬሽን ዱዱላ እና ማርች-ማርች በተባሉ የተደራጁ ቡድኖች በተለይም ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በመጡ ስደተኞች ላይ የሚፈጸሙትን የማስፈራራት፣ የጥቃት እና የኃይል እርምጃ ድርጊቶች አጥብቆ ያግዛል" ይላል።

ይህ አይነቱ ድርጊት በአፍሪካ የሰብአዊ እና ሰዎች መብቶች ቻርተር ላይ የተቀመጡ መሠረታዊ መብቶችን የሚጥስ እንደሆነም ኮሚሽኑ ገልጿል።

ከስደተኞች ጋር የተያያዙ ሕጎችን የማስፈጸም ኃላፊነት "የተፈቀደላቸው የመንግሥት ተቋማት ብቻ" እንደሆነ ያስታወሰው ኮሚሽኑ፤ የአገሪቱ መንግሥት ለስደተኞች የሚያደርገው ጥበቃ እንዲያጠናክር ጠይቋል።

"በሕገ ወጥ የሕግ ማስፈጸም እንቅስቃሴዎች" ውስጥ የሚሳተፉ ቡድኖችን "ለመበተን እና ለመግታት ጠንካራ እርምጃ" እንዲወስድም አሳስቧል።