የጣሊያኗ ጆርጂያ ሜሎኒ የቀኝ አክራሪ መንግሥት ሊመሠርቱ ነው

የፎቶው ባለመብት, QUIRINALE
የጣሊያን ቀኝ አክራሪ ፓርቲ መሪ ጆርጂያ ሜሎኒ መንግሥት ለመመሥረት በይፋ ፍቃደኝነታቸውን ገለጹ።
አንድ ቀኝ አክራሪ ብሔርተኛ ፓርቲ በጣሊያን መንግሥት ሲመሠርት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።
ፕሬዝዳንት ሰርጊዮ ማታሬላ ጆርጂያ ሜሎኒ መንግሥት እንዲመሠርቱ የጠየቁት ፓርቲያቸው ‘ብራዘለርስ ኦፍ ኢታሊ’ ምርጫ ማሸነፉነት ተከትሎ ነው።
ጆርጂያ ሜሎኒ የመጀመርያዋ የጣሊያን ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በይፋ ቃለ መሐላ የሚፈጽሙት በመጪው ቅዳሜ ነው።
ሥልጣን የሚረከቡት ደግሞ ጣሊያንን በአስቸጋሪው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ከመሯት ማሪዮ ድራጊ ነው።
የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል የሆነችው ጣሊያን በአውሮፓ ኅብረት አባላት ሦስተኛዋ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤት ናት።
ጆርጂያ ሜሎኒ በውጭ ፖሊሲ ረገድ ምንም ለውጥ እንደማያደርጉ ቃል ገብተዋል።
ሜሎኒ በነጭ ፊያት መኪና ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ተጉዘው ለአንድ ሰዓት ያህል ከፕሬዝዳንቱ ጋር ከተወያዩ በኋላ ከቤተ መንግሥት ወጥተው ካቢኔያቸውን አሳውቀዋል።
በካቢኔዋ ውስጥ የማቴዎ ሳልቪኒ ቀኝ አክራሪ ሊግ ፓርቲ እና የ86 ዓመቱ ሲልቪዮ በርለስኮኒ ፓርቲ ፎርዛ ኢታሊያ ተካቶበታል።
አወዛጋቢው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጋዳፊ ወዳጅ የነበሩት ሲልቪዮ በርልስኮኒ የፑቲን ቀንደኛ ደጋፊ መሆናቸውን የተናገሩበት የድምጽ ቅጂ ሾልኮ ከወጣ በኋላ በጣሊያን ጆርጂያ ሜሎኒ ሊመሠረቱት የነበረው መንግሥት መጠነኛ መንገጫገጭ ተፈጥሮበት ነበር።
የፓርቲዎቹ መሪዎች ከፕሬዝዳንት ማታሬላ ጋር አርብ ለ11 ደቂቃዎች ያህል ከተወያዩ በኋላ ጆርጂያ በሰጡት መግለጫ ጣሊያናዊያን በአዲሱ መንግሥት ሊተማመኑ ይገባል ብለዋል።
ጨምረውም፣ "አዲሱ መንግሥት በብቃት ችግሮችን የሚጋፈጥና መፍትሄ የሚሰጥ ይሆናል" ብለዋል።
ጆርጂያ ካዋቀሩት ካቢኔ ከ24 ሚኒስትሮች ውስጥ ስድስቱ ብቻ ሴቶች ናቸው።
ከነዚህም መሀል የቤተሰብና የወሊድ ምጣኔ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ኡጌንያ ሮሴላ ይገኙበታል። እኚህ ሴት ጽንስ ማቋረጥን የሚቃወሙ ናቸው።
አዲሱ የአካባቢ ጉዳዮች ሚኒስትር ሮቤርቶ ካልዴሮሊ በዘረኛ ንግግራቸው የሚታወቁ ሲሆን ከዚህ ቀደም የመጀመርያ ጥቁር የካቢኔ አባል የነበሩን ሰው ‘ዝንጀሮ’ ብለው የተሳደቡ ናቸው።
ሲልቪዮ በርልስኮኒ ምንም እንኳ በካቢኔው ባይካተቱም ይህን ጥምር መንግሥት ችግር ውስጥ ከተውት ቆይተዋል።
ይህም የሆነው የፑቲን ቀንደኛ ደጋፊ መሆናቸውን የተናገሩበት ድምጽ ቅጂ ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ ነው።
የ86 ዓመቱ በርልስኮኒ ቪላድሚር ፑቲን "20 ጠርሙስ ምን የመሰለ ቮድካ ለልደቴ ልኮልኛል" ካሉ በኋላ "እኔ ከፑቲን አምስት ምርጥ ወዳጆቹ አንዱ ነኝ" ሲሉ ተሰምቷል።
ከዚህም ሌላ በርልስኮኒ የዩክሬንን ፕሬዝዳንት ሲያወግዙ፤ ምዕራባዊያንን ሲያንቋሽሹና ፑቲንን ሲያንቆለጳጵሱ በሾለከው የድምጽ ቅጂ ይሰማል።
ሆኖም በርልስኮኒ ነገሩ ከአውድ ውጭ ተወስዶብኛል፤ ጣሊያንና ምዕራቡ በዩክሬን ጉዳይ የያዘውን አቋም እደግፋለሁ ሲሉ አስተባብለዋል።
ሌላው በጆርጂያ ሜሎኒ ካቢኔ ውስጥ የተካተቱት ማቴዎ ሳልቪኒም የረዥም ጊዜ የፑቲን አድናቂ ናቸው። ሆኖም ጆርጂያ ሜሎኒ ጥምር መንግሥት ለመመሥረት የግድ እርሳቸውን ማካተት ነበረባቸው።
ጆርጂያ ሜሎኒ የ45 ዓመት ሴት ሲሆኑ በጸረ ስደተኛ አቋማቸው የሚታወቁ ናቸው።
የመጀመርያ ሥራቸው የሚሆነው ጣሊያናዊያን የኃይል ወጪያቸውን ዝቅ ማድረግ ነው።
ከሊቢያ ወደ ጣሊያን የሚገቡ አፍሪካዊያን ስደተኞችን ለማቆም በሜዲትራኒያን የባሕር ኃይል አዘምታለሁ ብለዋል ሜሎኒ።
የሜሎኒ ፓርቲ መሥራችና አዲስ የሴኔቱ አፈ ጉባኤ የሆኑት ሰው፣ የፋሺስት ቤኒቶ ሞሶሎኒ ከፍተኛ አፍቃሪ ናቸው።
የጆርጂያ ሜሎኒ ፓርቲ፣ ብራዘርስ ኦፍ ኢታሊ ራሱ ከፋሽስቱ ሞሶሎኒ ዘመን የሚመዘዝ ታሪክ አለው።












