ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክና ኢንስታግራም በካናዳ በገጻቸው ላይ የሚቀርቡ ዜናዎችን ሊገድቡ ነው
ፌስቡክና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ በካናዳ በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ላይ የሚቀርቡ ዜናዎች ላይ ገደብ ሊጥል መሆኑን አስታወቀ።
ድርጅቱ ይህን ያለው የካናዳ ምክር ቤት አወዛጋቢ የሆነውን የኦንላይ ዜና ረቂቅ ሕግን ካጸደቀ በኋላ ነው።
ረቂቅ ሕጉ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ በገጻቸው ላይ ለሚታተሙ ይዘቶች ለዜና አሳታሚዎች እንዲከፍሉ ያስገድዳል።
ሜታ እና ጉግል ለተወሰኑ ካናዳውያን ዜና የሚገድብ ሙከራ እያደረጉ ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ 2021 በተመሳሳይ ሕግ ምክንያት አውስትራሊያውያን ተጠቃሚዎችም በፌስቡክ ላይ ዜናዎችን እንዳያዩ እና እንዳያጋሩ ተገድበው ነበር።
የካናዳ ምክር ቤቱ ሐሙስ ዕለት ያሳለፈው የኦንላይን ዜና ሕግ እንደ ሜታ እና ጉግል ያሉ መድረኮች ለዜና ይዘቶች ከዜና ድርጅቶች ጋር የንግድ ስምምነት እንዲያደርጉ እና እንዲከፍሉ ያስገድዳል።
ሜታ ሕጉን "የማሕበራዊ ሚዲያ መድረኮቹን አሠራር እውነታ ችላ ያለ መሠረታዊ ጉድለት ያለበት” ብሎታል።
ሆኖም ሕጉ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ፌስቡክ እና ኢንስታግራም በካናዳ ላሉ ተጠቃሚዎቹ ዜና ማቅረቡን እንደሚያቆም ድርጅቱ ሐሙስ እለት አስታውቋል።
የሜታ ቃል አቀባይ “ እኛ ላለጠፍነው የዜና ሊንኮች እና ይዘቶች እንድንከፍል የሚጠይቀው እንዲሁም በርካታ ደንበኞች የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹን የሚጠቀሙበት ምክንያት ያልሆነው የሕግ ማዕቀፍ ዘላቂነት የሌለውና የማይሰራ ነው " ሲል ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ድርጅቱ ጨምሮም በካናዳ ዜናን በተመለከተ የተደረገው ለውጥ በሌሎች አገልግሎቶቹ ላይ ተፅዕኖ አይፈጥርም ብሏል።
ጉግልም በበኩሉ ሕጉ አሁን ላይ ባለው አግባብ “የማይሠራ" ያለው ሲሆን ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ከመንግሥት ጋር እየሠራ እንደሆነ ገልጿል።
የፌደራል መንግሥት በበኩሉ የኦንላይን ዜና ሕጉ ፣ ለካናዳውያን የዲጂታል ዜና ገበያ ያለውን ፍትሃዊነት የሚያሳድግ ነው፤ እየተንገዳገዱ ያሉት የዜና ድርጅቶች በማኅበራዊ መድረኮቹ ለሚያቀርቧቸው ዜናዎች እና ሊንኮች ፍትሃዊ የሆነ ክፍያ እንዲያገኙም የሚፈቅድ ነው ብሏል።
ገለልተኛ የሆነው የምክር ቤቱ በጀት ተመልካች ትንታኔ የዜና ንግዱ ከዲጂታል መድረኮች በዓመት 250 ሚሊየን ዶላር ሊያገኝ እንደሚችል ገምቷል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የካናዳ የቅርስ ሚኒስትር ፓብሎ ሮዲሪጉዝ፣በቴክኖሎጂ መድረኮቹ የሚካሄደው ሙከራ “ ተቀባይነት የሌለው" እና "ስጋት" መሆናቸውን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
በአውስትራሊያ ፌስቡክ ከመንግሥት ጋር ንግግር ካደረገ በኋላ በተደረገ የሕግ ማሻሻያ ለተጠቃሚዎቹ የዜና ይዘቶችን እንደገና ማቅረብ ጀምሯል።
ሐሙስ ዕለት የሚኒስትር ሮደሪጊዝ ቢሮ ከጉግል እና ከፌስቡክ ጋር በዚህ ሳምንት መነጋገሩንና ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ማቀዱን ቢገልጽም መንግሥት ግን ሕጉን ተግባራዊ አደርጋለሁ ብሏል።
“ የዜና መድረኮቹን በተመለከተ መንግሥት ለካናዳውያን ካልቆመ ማን ሊቆም ይችላል?” ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
የሚዲያ ኢንደስትሪ ቡድንም ሕጉ መጽደቁ ያለውን የዜና ገበያ ፍትሃዊ ለማድረግ አንድ እርምጃ ነው ብሎታል።
የሚዲያ ኢንደስትሪ ግሩፕ የሆነው የኒውስ ሚዲያ ካናዳ ፕሬዚደንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፖል ዲጋንም በመግለጫቸው፣ " ካናዳውያን እውነተኛ ጋዜጠኝነትን ከትክክለኛ ጋዜጠኞች ማግኘት ይፈልጋሉ። ይህ ለዲሞክራሲያችንም ወሳኝ ነው፣ ነገር ግን ገንዘብ ያስከፍላል።” ብለዋል።
የኦንላይን ዜና ሕጉ በስድስት ወራት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል።