በኢትዮጵያ እና በሌሎች አገራት ለሚከሰተው የቺኩንጉንያ በሽታ አሜሪካ ክትባት አጸደቀች

ታትሟል

የአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር ባለሥልጣን ቺኩንጉንያ ለተባለው በሽታ መከላከያ የመጀመሪያው ክትባት አጸደቀ።

በወባ ትንኝ የሚተላለፈው ቺኩንጉንያ “ለዓለም የጤና ስጋት እየሆነ የመጣ በሽታ” ተብሎ የሚገለጽ ሲሆን፤ ከጥቂት ዓመታት በፊትም በምሥራቅ ኢትዮጵያ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ በርካታ ሰዎችን አጥቅቶ ነበር።

የአሜሪካው ተቋም ለክትባቱ ፍቃድ መስጠቱ የክትባቱ ሥርጭት በመላው ዓለም በፍጥነት እንዲሰራጭ ያስችላል ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት በቺኩንጉንያ በሽታ የተያዘን ሰው ለማከም የሚረዳ ምንም አይነት መድኃኒት የለም።

እየተጠናቀቀ ባለው በአውሮፓውያኑ 2023 በመላው ዓለም 440 ሺህ ሰዎች በበሽታው የተጠቁ ሲሆን፣ 350 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉ ሪፖርት ተደርጓል።

ደቡብ አሜሪካ እና ደቡብ እስያ በበሽታው የተጠቁ በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው የዓለማችን ክፍሎች ናቸው።

ቫልኔቫ በተሰኘው የፈረንሳይ ክትባት አምራች ኩባንያ የተመረተው እና ኢክቺንግ የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ የመከለከያ ክትባት፤ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ እና ለበሽታው ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እንዲሰጥ ፍቃድ ማግኘቱን የአሜሪካ የምግብ እና መድኃኒት ባለሥልጣን (ኤፍዲኤ) አስታውቋል።

“በቺኩንጉንያ ቫይረስ መጠቃት ለከፍተኛ ሕመም ከማጋለጡም በላይ በተለይ ዕድሜያቸው በገፉ እና የቀደመ የጤና ችግር ባለባቸው ላይ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ የጤና ችግርን ያስከትላል” ብለዋል የኤፍዲኤ አጋር የሆኑት ፒተር ማርክስ።

ከእአአ 2008 ጀምሮ በመላው ዓለም በቺኩንጉንያ በሽታ መያዛቸው ሪፖርት የተደረጉ ሰዎች ቁጥር ከ5 ሚሊዮን እንደማያንስ የተገለጸ ሲሆን፣ ከአራት ዓመታት በፊት በምሥራቅ ኢትዮጵያ በሽታው በወረርሺኝ መልክ በተዛመተበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሕመም ተጠቅተው ነበር።

በበሽታው የተያዘ ሰው ከሚያሳያቸው የተለመዱ መልክቶች መካከል የጡንቻ ሕመም፣ ሽፍታ እና ራስ ምታት ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ በበሽታው ምክንያት ሊመጣ የሚችለው የመገጣጠሚያ ሕመም ደግሞ ለዓመታት ሊቆይ ይችላል።

የቺንኩንጉንያ ቫይረስ የሚሸከሙ የወባ ትንኞች ቆላማ በሆኑ የአፍሪካ፣ ደቡብ ምሥራቅ እስያ እና በመካከለኛው አሜሪካ ስለሚገኙ በእነዚህ አካባቢ ያሉ ሰዎች ለበሽታው የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

ከአውሮፓ የበሽታ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ማዕከል የተገኘ አሃዝ እንደሚያሳየው፣ በዚህ ዓመት ብራዚል ከፍተኛውን በበሽታው የተጠቁ ሰዎች መገኛ አገር ሆናለች።

እንደ ተቋሙ ከሆነ በብራዚል 218 ሺህ ሰዎች በበሽታው የተያዙ ሲሆን፣ በሕንድ ደግሞ ከ93 ሺህ ያላሱ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተው ነበር።