አሜሪካ በአውሮፓ ያላትን የጦር ሃይል ለማሳደግ ወሰነች

አሜሪካ በመላው አውሮፓ ያላትን ሃይል በተለይም በምስራቃዊ አውሮፓ ያላትን ሃይል ለማጠናከር ወስናለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ኔቶ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ለከፈተችው ወረራ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለውን አዲስ “መሰረታዊ ለውጥ” ማድረጉን ማስታወቁን ተከትሎ አሜሪካ በመላው አውሮፓ የሚገኘውን ወታደራዊ ኃይሏን ለመጨመር መወሰኗን አስታወቀች።  

በፖላንድ የሰራዊቷን ዋና መስሪያ ቤት እንደምትከፍት ያስታወቀችው አሜሪካ አዳዲስ የጦር መርከቦችን ወደ ስፔን፣ ተዋጊ ጄቶችን ወደ እንግሊዝ እና የምድር ጦሯን ወደ ሮማኒያ ትልካለች።  

ፕሬዘዳንት ባይደን ኔቶ “ከምንጊዜውም በበለጠ አሁን ያስፈልገናል” ብለዋል።  የኔቶ ኃላፊ የንስ ስቶልተንበርግ በበኩላቸው ኔቶ ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ ትልቁን ለውጥ እያመጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

ለሩሲያ ወረራ ምላሽ የሚሰጠው አዲሱ እቅድ አሁን ያለውን በተጠንቀቅ ያሉ ወታደሮችን ቁጥር ከ40 ሺህ ወደ 300 ሺህ ያሳድጋል።  

ፐሬዘዳንት ባይደን በማድሪድ በተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ላይ ኔቶ "በሁሉም አቅጣጫ በሁሉም ጎራ - መሬት፣ አየር እና ባህር" ይጠናከራል ብለዋል። 

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩላቸው የአገራቸውን ሃይል ለኔቶ የበለጠ ክፍት እንዲሆን መደሩጉን እና ተጨማሪ የጦር መርከቦች፣ ተዋጊ ጄቶች እና የመሬት ሃይሎች በተጠባባቂነት መቀመጣቸውንም አስታውቀዋል።

ነገር ግን ዝርዝር ቁጥሮች ወታደራዊ ሚስጥር በመሆናቸው ምክንያት መገለጽ እንደማይችሉ ተናግረዋል።

አሜሪካ በመላው አውሮፓ ያላትን ሃይል ለማጠናከር ብታስብም በተለይም በምስራቃዊ አውሮፓ ውስጥ አዲሱ የ 5 ኛው ሰራዊት ኮርፖሬሽን ቋሚ ዋና መስሪያ ቤት እንደሚቀመጥ ተመልክቷል። 

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሚስተር ባይደን የሕብረቱን ቁርጠኝነት ደጋግመው በመግለጽ የግዛቱን “እያንዳንዱን ኢንች እንከላከላለን’’ ያሉ ሲሆን አክለውም “በአንዳችን ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሁሉም ላይ የሚደረግ ጥቃት ነው ስንል በቁርጠኝነት ነው’’ ሲሉም ተደምጠዋል።  

አዳዲሶቹ እርምጃዎች በስፔን የሚገኙ የአሜሪካን የባህር ኃይል አጥፊዎችን ከአራት ወደ 6 ማሳደግ፣ ሁለት ተጨማሪ የ F-35 ድብቅ አውሮፕላኖች ቡድን ወደ እንግሊዝ ብሎም በጀርመን እና በጣሊያን ተጨማሪ የአየር መከላከያዎችን ማቆም ያጠቃልላሉ።  

እንዲሁም ዩናይትድ ኪንግደም በኢስቶኒያ የነበራትን ሃይል በእጥፍ በማሳደግ አሁን ቁጥርሩን ከ1 ሺህ 600 በላይ አድርሳለች።  

በጉባኤው ላይ የኔቶ መሪዎች ቀደም ሲል ገለልተኛ ሆነው የቆዩትን የኖርዲክ አገራቱን ማለትም ፊንላንድ እና ስዊድን ወደ ጥምረቱ ለመቀበል ተስማምተዋል። ነገር ግን አባልነታቸውን  በ30ዎቹም የኔቶ አባል አገራት መንግሥታት መጽደቅ ይጠበቅበታል።  

ፕሬዘዳንት ባይደን ይህ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የማይፈልጉት እርምጃ ነው ያሉ ሲሆን ፑቲን ዩክሬንን የመውረር ስልታቸው መልሶ እየጎዳቸው ያለ ጉዳይ ነው ብለዋል። 

የኔቶ ዋና ፀሃፊ ስቶልተንበርግ ፊንላንድ እና ስዊድን ወታደራዊ ሕብረቱን እንዲቀላቀሉ በይፋ መጋበዛቸውን ገልጸው ይህም እስካሁን ከነበሩት ጋር ሲነጻጸር “ፈጣኑ የመቀላቀል ሂደት” መሆን ገልፀው ግስጋሴው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። 

ሁለቱ አመልካቾች አሁን የኔቶ መስፈርቶችን በፖለቲካ፣ በህግ እና በጦር ሃይላቸው ውስጥ እንደሚያሟሉ ማሳየት አለባቸው። ይህ ለኖርዲክ ሀገራት በአንፃራዊነት ቀላል እንደሚሆን ይጠበቃል። 

ስቶልተንበርግ እንዳሉት ዩክሬን የሩሲያን ጥቃት ለመጋፈጥ በሕብረቱ የሚደረገውን ድጋፍላይ መተማመኗን መቀጠል ትችላለች ብለዋል ። 

አባል ሀገራት ለዩክሬን "አጠቃላይ የእርዳታ ፓኬጅ" ለማቅረብ የተስማሙ ሲሆን ይህም ነዳጅ፣ የሕክምና ቁሳቁሶች፣ የሰውነት መከላከያ መሳሪያዎች፣ ፀረ-ድሮን ስርዓቶች እና ፈንጂዎችን ለመከላከል የሚረዱ መሳሪያዎችን ያካትታል።