የሱዳን ጦር ለተቃውሞ ወደ ቤተመንግሥት ሲያመሩ የነበሩ ተቃዋሚዎችን በአስለቃሽ ጭስ በተነ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሱዳን ጦር የተቃውሞ ድምጽ ለማሰማት ወደ ፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ሲያመሩ የነበሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎችን በአስለቃሽ ጭስ በተነ።
የአገሪቱን ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የገታውን መፈንቅለ መንግሥት አንደኛ ዓመት በማስመልከት በመላ አገሪቱ ተቃውሞው እየተካሄደ ነው።
የጦር ኃይሉ አዛዥ አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ስልጣን ከያዙ ወዲህ በየሳምንቱ በሚባል ደረጃ የጸረ መፈንቅለ መንግሥት ሰልፎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
የጸጥታ ኃይሎች ባለፈው ዓመት ከ100 በላይ ተቃዋሚዎችን ገድለዋል በሚል ይከሰሳሉ።
ጦሩ ስልጣኑን መያዙ ለጋሾች ዕርዳታ እንዲያቋርጡ ያደረጋቸው ሲሆን ይህም የሱዳን ኢኮኖሚም እንዳይረጋጋ አድርጎታል ተብሏል።
ማክሰኞ ዕለት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ወደ ጎዳና መውጣታቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ተቃዋሚዎቹ ካርቱም ወደሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግሥት ሲያቀኑ የጸጥታ ኃይሎች ጣልቃ በመግባት አስለቃሽ ጪስ በመጠቀም ለመበተን ሞክረዋል።
ለቤተ መንግስቱ አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀራቸው ጀንበር ከመጥለቋ በፊት ተቃዋሚዎቹ መበተናቸው ታውቋል።
እስከ ምስሽ 12 ሰዓት ድረስ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ኔትብሎክስ የተሰኘው ተቆጣጣሪ ቡድን አስታውቋል።
በጸጥታ ኃይሎች መኪና ተገጭቶ ኡምዱሩማን ላይ አንድ ግለሰብ ሕይወቱ ማለፉን ተቃውሞን ሚደግፉ የሱዳን ዶክተሮች ማዕካለዊ ኮሚቴ አስታውቋል። ይህም በታቃውሞ ምክንያት የሞቱትን ሰዎች ቁጥር 119 አድርሶታል።
ከዓመት በኋላም የጦሩ አመራሮች ጠቅላይ ሚንስትር እስካሁን አልሾሙም። በ2019 ከስልጣን የወረዱት ኦማር አል-በሽር ደጋፊዎች ወደ ስልጣን መጥተዋል።
አልበሽር ወደ ስልጣን ካመጣቸው መፈንቅለ መንግሥት እና ከዳርፉር ጦርነት ጋር በተያያዝ ጉዳያቸውን በእስር ቤት ሆነው እየተከታተሉ ነው።
መንግሥት ሲቋቋም ስልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ የገለጹት የጦሩ አመራሮች 'ፎርስስ ኦፍ ፍሪደም ቼንጅ' ከተባለው እና ከመፈንቅለ መንግሥቱ በፊት ስልጣን ከሚጋራው ጥምረት ጋር ውይይት እያደረጉ ነው። ብዙ ተቃዋሚዎች ውይይቱን አይቀበሉትም።












