አንቶኒ ብሊንከን ስለሰላም ንግግሩ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መነጋገራቸው ተገለጸ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ እና የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ እና የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን
ታትሟል

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ስላለው የሰላም ውይይት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መነጋገራቸውን ገለጹ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትናንት ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ ብሊንከን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር የተነጋገሩት ግጭቱ በአስቸኳይ ማቆምን በተመለከተ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ብሊንከን በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኬንያው ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ እና ከደቡብ አፍሪካው የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር ፓንዶር ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል።

"ግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝም ከአፍሪካ ኅብረት ጋር መምከሬን እቀጥላለሁም ብለዋል" የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።

ለግጭቱ ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ አይሆንም ያሉት አንቶኒ ብሊንከን፣ ይህ የሰላም ድርድር ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘላቂ የሆነ ሰላም ለማምጣት ተስፋ ሰጭ መንገድ መሆኑንም በመግለጫቸው አስታውቀዋል።

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ ኃይሎች መካከል የሚደረገው የሰላም ንግግር ትናንት ጥቅምት 15፣2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ መጀመሩ ተገልጿል።

የአፍሪካ ኅብረት ትናንት ጥቅምት 15፣ 2015 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ አሜሪካ ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና ምሥራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑን አስታውቋል።

የሰላም ንግግሩን በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሐመት፣ የሰላም ንግግሩ ተሳታፊዎች ለገቡበት ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመስጠት ኅብረቱ የሚያደርገውን ጥረት መጀመሩን በመግለጫቸው አስታውቀው ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች እየተካሄደ ባለው የሰላም ንግግር ሊደራደሩባቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች በይፋ ባይገልጹም፤ የትግራይ ከፍተኛ አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት፣ ግጭት በአስቸኳይ ማስቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ማስወጣት የሚሉት በንግግሩ የሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የፌደራል መንግሥት ግን ከዚህ ቀደም "ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ" ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር አሜሪካ እንደምትቀበለው አንቶኒ ብሊንከን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለግጭቱ የመጨረሻ እልባት ለማግኘት በዚህ ድርድር የተሳተፉ ተደራዳሪ ልዑካን በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲነጋገሩም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።

ግጭቱን በአስቸኳይ ማቆም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ የገለጸው መግለጫው፣ ተደራዳሪዎቹ በጦርነቱ ለተጎዱ እና ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ፣ የሰላማዊ ሰዎች ደኅንነት ለመጠበቅ እርምጃ እንዲወስዱ እንዲሁም የኤርትራ ኃይሎች ከሰሜን ኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ከስምምነት እንዲደርሱም ጥሪ አቅርበዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረውም፣ ደቡብ አፍሪካ ይህንን የሰላም ድርድር በማዘጋጀቷ አድናቆታቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አደራዳሪዎቹን የአፍሪካ ኅብረት ልዩ መልዕክተኛ ኤሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዚደንት ማላምቦ ንግኩካ እና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታም እንደግፋለን ብለዋል።