ከደቡብ አፍሪካው ድርድር ባሻገር በትግራይ ምን እየሆነ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜን ኢትዮጵያው የርስ በርስ ጦርነት እየተዋጉ ያሉት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች ወኪሎቻቸውን ደቡብ አፍሪካ ልከው ለንግግር ቢቀመጡም ጦርነቱ በትግራይ ተጠናክሮ ስለመቀጠሉ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።
ባለፉት ቀናት የፌደራል መንግሥቱ ጥምር ጦር እንደ አድዋ፣ ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረም ያሉ የትግራይ ከተሞችን ስለመቆጣጠሩ በስፋት ተዘግቧል።
የፌደራል መንግሥቱ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ከሁለት ቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በስም ያልጠቀሳቸውን “ቁልፍ” የሚባሉ የትግራይ ከተሞችን መቆጣጠሩን ቀጥሏል ብሎ ነበር።
የፌደራሉ መንግሥት በኤርትራ ሠራዊት ታግዞ በትግራይ ኃይሎች ላይ የሚያካሂደውን ዘመቻ አጠናክሮ ይቀጥል እንጂ፤ ለሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የሰላም ንግግር ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ተጀምሯል።
ይህ በስፋት ሲጠበቅ የቆየው የሰላም ንግግር ከጥቅምት 15 ጀምሮ እስከ እሁድ ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም. ቀጥሎ እንደሚካሄድ የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል።
የትግራይ ኃይሎች ‘እየተበተኑ ነው’ እስከ ‘ትግራይ የገባ አይወጣም’
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ የትግራይ ኃይሎች ተዋጊዎች “በሁሉም ግንባር እጅ እየሰጡና እየተበተኑ ነው” ብሎ ነበር።
መከላከያ "የህወሓት ታጣቂዎች መከላከያ ወደተቆጣጠራቸው የትግራይ አካባቢዎችና ወደ አጎራባች ክልሎች በመሄድ እጃችሁን በሰላም ስጡ" ሲል መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፤ እጅ ለሚሰጡ ታጣቂዎችም “አስፈላጊው እንክብካቤ እንዲደረግ መመሪያ ተላልፏል” ሲልም አክሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ትግራይ የገቡት የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጥምር ኃይል አባላት “መቀበሪያቸው ትግራይ” ትሆናለች ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።
ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል፤" የትግራይ ኃይል ጠላቶቹን የማሸነፍ ሙሉ አቅም አለው" ብለዋል።
ደብረጽዮን ጥቅምት 14/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ “የትግራይ ሠራዊት የሁለት አገር ጦር ገጥሞ ጀግንነቱን አስመስክሯል” ካሉ በኋላ “ትግሉ ይቀጥላል” ብለዋል።
የደቡብ አፍሪካው ንግግር
ትናንት በደቡብ አፍሪካ የተጀመረውን የሰላም ንግግር በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ፣ የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ፑምዚሌ ማላምቦ-ናኩክ እንደሚያስተባብሩት ተገልጿል።
በዚህ ድርድር ላይ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የምስራቅ አፍሪካ በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) ደግሞ በታዛቢነት እየተሳተፉ መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት አስታውቋል።
የአፍሪካ ኅብረት ተፋላሚ ኃይሎች ግጭት አቁመው ልዩነቶቻቸው በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
ሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች ሊደራደሩባቸው የሚችሏቸውን ጉዳዮች በይፋ ባይገልጹም፤ የአፍሪካ ኅብረት እና ምዕራባውያን ግን ለግጭቱ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል።
ህወሓት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር በሚደረገው ውይይት የትግራይ ኃይሎች የሚያነሷቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች ግጭት በአስቸኳይ ማስቆም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እና የኤርትራ ኃይሎች ከትግራይ ማስወጣት የሚሉት ስለመሆናቸው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ሕይወት ገልጸው ነበር።
የፌደራል መንግሥት በዚህ ድርድር ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ ያለው ነገር ባይኖርም፤ ከዚህ ቀደም ግን "ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ" ለንግግር ዝግጁ መሆኑን ሲገልጽ ቆይቷል።












