በተጭበረበረ ሰነድ ለ17 ዓመት አውሮፕላን ያበረረው 'ካፒቴን' ተያዘ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞው ኤር ካናዳ አብራሪ ለ17 ዓመታት ተገቢው ፈቃድ ሳይኖረው በሺህዎች የሚቆጠሩ መንገደኞችን ማመላለሱን ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ፖሊስ የ59 ዓመቱ የኦንታሪዮ ነዋሪ የሆነው ጄፍሪ በአውሮፓውኑ 2009 ካፒቴን ከሆነ ጊዜ አንስቶ በተጭበረበረ ሰነድ አውሮፕላን ያበር እንደነበር ደርሶበታል።

አሁን በተለያዩ የማጭበርበር ወንጀሎች ላይ በመሳተፍ ክስ አንደሚመሠረትበት ተገልጿል።

ኤር ካናዳ ባለፈው ዓመት ሐሰተኛ ሰነዶቹ እንደታወቁ ወድያውኑ ከሥራው መታገዱን ይፋ አድርጓል።

አየር መንገዱ "ኩባንያው በፈቃደኝነት ጉዳዩን ለካናዳ ትራንስፖርት አሳውቋል" ሲል አስታውቋል።

አየር መንገዱ አክሎም የመንገደኞች ደኅንነት በጭራሽ አደጋ ላይ አለመውደቁን እና ሁሉም አብራሪዎች በየስድስት ወሩ የብቃት ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል ሲል ተናግሯል።

ምክትል የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኒክ ሚሊኖቪች ግለሰቡ በኤር ካናዳ ላለፉት 27 ዓመታት አውሮፕላን ሲያበር እንደነበር ገልጸው ሥራ የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1998 መሆኑን ተናግረዋል።

ፓይለቱ ከ2009 ጀምሮ ካፒቴን ወደ መሆን ካደገ በኋላ ሰነዶቹን ማጭበርበሩ ተገልጿል።

በካናዳ ሕግ መሠረት አውሮፕላን አብራሪዎች ካፒቴን የሚለውን ማዕረግ ለማግኘት በርካታ የጽሑፍ ፈተናዎችን በማለፍ የትራንስፖርት የአውሮፕላን አብራሪነት ፈቃድ (ኤቲፒኤል) ማግኘት አለባቸው።

የፖሊስ አዛዡ ሚሊኖቪች "ይህ ልክ ዶክተሮች አጠቃላይ ሕክምና ላይ እንዲሰማሩ ፈቃድ ተሰጥቷቸው በቢሯቸው የአንጎል ቀዶ ሕክምና ከመስጠት ጋር ተመሳሳይ ነው" ብለዋል።

ላለፉት 17 ዓመታት ዎል ያለ ትክክለኛ ሰነድ በርካታ የቦይንግ አውሮፕላኖችን እና ከ900 በላይ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ በረራዎችን በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ደመወዝ ተቀብሏል።

ባለሥልጣናት የተጭበረበረ ሰነድ መኖሩ የተደረሰበት ባለፈው ዓመት የተለመደው ምዘና ሲካሄድ መሆኑን አስታውቀዋል።

የግለሰቡ የአብራሪነት ፈቃድ ላይ ወጥ ያልሆኑ ነገሮች መኖራቸው ከታወቀ በኋላ ለካናዳ ትራንስፖርት ባለሥልጣን፣ ለካናዳ የፌደራል ትራንስፖርት ቢሮ ጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲያደርጉ ተላልፎ ተሰጥቷል።

የቶሮንቶ አካባቢ ፖሊስ ወዲያውኑ በፖል ላይ የወንጀል ምርመራ የጀመረ ሲሆን፣ ፈቃዱ ላይ ባደረገው ምርመራ እንዲሁም በመኖሪያ ቤቱ ላይ በተደረገ ፍተሻ ሰነዱ የተጭበረበረ መሆኑን ደርሶበታል።

ዎል ባለፈው ሳምንት በማጭበርበር፣ ሐሰተኛ ሰነድ በማዘጋጀት፣ ሐሰተኛ ማኅተም ይዞ በመገኘት በአጠቃላይ በሰባት ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶበታል።

ኤር ካናዳ አብራሪው ሙሉ ሥልጠና የወሰደ እና የንግድ አውሮፕላኖችን ለማብረር የሚያስችል ፈቃድ ያለው መሆኑን ገልጾ፤ ነገር ግን በካናዳ ሕግ መሠረት ከአገሪቱ የትራንስፖርት መሥሪያ ቤት የሚሰጠው ፈቃድ (ኤቲፒኤል) የለውም ብሏል።

አየር መንገዱ በመግለጫው ላይ "ጉዳዩን በሚገባ እንከታተለዋለን" ካለ በኋላ ያሉት አብራሪዎች ላይ ማጣራት ማድረጉን እና ተመሳሳይ ችግር አለማግኘቱን ይፋ አድርጓል።

ምክትል የፖሊስ አዛዡ አብራሪው ለዓመታት ሳይታወቅበት ስለመቆየቱ ሲጠየቁ አታላዮች "በማጭበርበር እና በማታለል. . .በጣም ጎበዝ ናቸው" ሲሉ መልሰዋል።

"ማጭበርበር ለዓመታት ሳይታወቅ መዝለቁ አዲስ ነገር አይደለም" ያሉት ምክትል አዛዡ "መያዙ አይቀርም፤ ያኔ ነው እኛ የምንመጣው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

ጄፍሪ ዎል በሰኔ ወር መጨረሻ ገደማ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ታውቋል።