እንግሊዛዊው የደኅንነት አማካሪ ዩክሬን ውስጥ በሚሳዔል ጥቃት ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሮይተርስ ለተሰኘው የዜና ወኪል ይሰራ የነበረው እንግሊዛዊ ዩክሬን ውስጥ በሚሳዔል ጥቃት መገደሉን ድርጅቱ ይፋ አደረገ።
ብሪታኒያዊው ግለሰብ ቅዳሜ ዕለት በሰተነዘረ የሚሳዔል ጥቃት ባረፈበት ሆቴል ውስጥ እንዳለ መገደሉን ነው ሮይተርስ ያሳወቀው።
የደኅንነት አማካሪ ሆኖ ለሮይተርስ ያገለግል የነበረው ራያን ኢቫንስ፤ ክራማቶርስክ በተሰኘችው ከተማ ሳፋየር ሆቴል ከሌሎች አምስት የሮይተርስ አባላት ጋር ነበር።
ክራማቶርስክ በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ብትሆንም በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ባለው ጦርነት ከፍተኛ ጥቃት ከሚፈጸምባት ሥፍራዎች መካከል ናት።
የዩክሬን ባለሥልጣናት ሆቴሉ ጥቃት የደረሰበት ከሩሲያ በተሰነዘረ ሚሳዔል ምክንያት ነው ሲሉ የሩሲያ ባለሥልጣናት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የሮይተርስ የዜና ወኪል ቃል አቀባይ በለቀቁት መግለጫ በኢቫንስ ሞት ድርጅቱ “እጅግ ማዘኑን” ገልፀዋል።
“ስለደረሰው ጥቃት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት እያደረግን ነው፤ ከክራማቶርስክ ባለሥልጣናት ጋር አብረን እየሰራን ነው፤ አልፎም ባልደረቦቻችን እና ቤተሰቦቻቸውን እየደገፍን እንገኛለን” ይላል መግለጫው።
“ለራያን ቤተቦችን እና ወዳጅ ዘመዶች መፅናናትን እንመኛለን። ራያን በርካታ ጋዜጠኞቻችንን በማገዘ በመላው ዓለም ተዟዙሯል። እሱን ማጣታችን ከባድ ነው።”
ሮይተርስ ጨምሮ እንዳስታወቀው ሁለት የቡድኑ አባላት በጥቃቱ በደረሰባቸው ጉዳት ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸውን እንዲሁም አንድ ግለሰብ እጅግ ከባድ ጉዳት እንደደረሰበት አሳውቋል።
የዩክሬን ብሔራዊ ፖሊስ በበኩሉ ከ19 ሰዓታት ፍለጋ በኋላ እሑድ ዕለት በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር አመሻሹን 12፡00 ገደማ የ40 ዓመቱ ብሪታኒያዊ ራያን አስክሬን ከፍርስራሽ ውስጥ ተገኝቷል ብሏል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በቴሌግራም ገፃቸው በለቀቁት መልዕክት ለብሪታኒያዊው ወዳጅ ዘመዶች “መፅናናትን እመኛለሁ” ብለዋል።
“ይህ ነው እንግዲህ በየቀኑ የምንጋፈጠው የሩሲያ የሽብር ተግባር” ሲሉ አክለዋል።
ሮይተርስ በጥቃቱ ምክንያት ሙሉ በሙሉ የወደመውን ሆቴል ሕንፃ የሚያሳይ ምስል ለቋል። የእሣት አደጋ ሠራተኞች በፍርስራሹ ውስጥ ነብስ ለማዳን ሲታገሉ ይታያሉ።
ሆቴሉ ኢስካንዴር-ኤም በተባለ አጭር ርቀት ተጓዥ ሚሳዔል ሳይመታ እንዳልቀረ የዩክሬን አቃቤ ሕግ ቢሮ አስታውቋል።
ክራማቶርስክ በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ካሉ የዩክሬን ግዛቶች 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን በተደጋጋሚ ጥቃት የሚደርስባት እንዲሁም ታዋቂዋ ዩክሬናዊት ፀሐፊ ቪክቶሪያ አሜሊናን ጨምር ሌሎች ንፁሀን የተገደሉባት ከተማ ናት።
ባለፉት ወራት የሩሲያ ጦር ቀስ በቀስ በምስራቃዊው የዩክሬን ክፍል ያለውን ግዛት እያሰፋ ሲሆን ዩክሬን በቅርቡ ወደ ሩሲያ ድንበር ገብታ ያደረሰችው ጥቃት የሩሲያ ወታደሮች እንዲያፈገፍጉ ለማድረግ የተደረገ እርምጃ ነው ተብሏል።












