የትግራይ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ከኃላፊነት ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ አነሱ

የፎቶው ባለመብት, Supreme Court of Tigray
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፀጋይ ብርሃነ እና ምክትላቸው አቶ ገብረአምላክ የዕብዮ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ያቀረቡትን ጥያቄ በመተው፤ በአመራርነት ለመቀጠል መወሰናቸው ተገለጸ።
ሁለቱ አመራሮች ከቀናት በፊት ያቀረቡትን ጥያቄ ያነሱት ትናንት ረቡዕ ሰኔ 19፤ 2016 ዓ.ም. ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር ባደረጉት ንግግር፤ ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ በማግኘታቸው እንደሆነ የጠቅላይ የፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መለስ አሸብር ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተያዘው ዓመት መጀመሪያ ላይ የትግራይ ክልል ፍርድ ቤቶች እንዲመሩ የተሾሙት ሁለቱ አመራሮች፤ ከስልጣን ለመልቀቅ መወሰናቸውን ያስታወቁት ሰኞ ዕለት ለፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በጻፉት ደብዳቤ ነበር። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት “የተሰጠንን ከባድ ኃላፊነት እና ተልዕኮ አንግበን በአመራርነት ለመቀጠል እና የጀመርነውን የለውጥ አቅጣጫ ለማሳካት የሚያስችል ሁኔታ ማግኘት አልቻልንም” በሚል ነበር።
አመራሮቹ የመልቀቂያ ጥያቄያቸው ምላሽ እስከሚያገኝ ድረስ በስራ ላይ እንደሚቆዩም በደብዳቤው ላይ ጠቅሰው ነበር። ይህ ጥያቄ ከሁለት ቀናት በኋላ በትናንትናው ዕለት የክልሉ ጊዜያዊ መስተዳደር ፕሬዝዳንት እና ሁለቱ አመራሮች በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውይይት ማድረጋቸውን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ መለስ ገልጸዋል።
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከውይይቱ በኋላ ባወጣው መግለጫ፤ የተደረገው ንግግር በሁለቱ አመራሮች የመልቀቂያ ጥያቄ እንዲሁም “መላው የፍርድ ቤት ማህበረሰብ ባነሳቸው ጥያቄዎች” ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውቋል። ውይይቱ፤ “ፍርድ ቤት ሶስተኛ የመንግስት አካል በመሆኑ የሚገባውን እውቅና፣ ክብደት እና ክብር በመስጠት” የተከናወነ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
“መንግስታዊ ትኩረት እና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ በታመነባቸው” ጥያቄዎች ላይ በተደረገው በዚህ ውይይት፤ “በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የተወሰኑ ህጋዊ ውሳኔዎችን እና የተለዩ ቀጣይ አቅጣጫዎች” ተቀባይነት እንዳገኙ በመግለጫው ላይ ሰፍሯል።
የጠቅላይ የፍርድ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መለስ እንደሚያስረዱት፤ የክልሉ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ከዚህ ቀደም ውሳኔ ከሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ “ከጥቅማ ጥቅም” ጋር የሚገናኝ ነው። ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ጥናት ተደርጎ እንደነበር የጠቀሱት አቶ መለስ፤ በጥናቱ መሰረት “የሲቪል ሰራተኞች ደመወዝ ማሻሻያ” ተወስኖ እንደነበር አስታውሰዋል።
በትናንቱ ውይይት ላይ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤው የተወሰኑት ውሳኔዎች “ህጋዊነታቸውን ጠብቀው እንደሚሄዱ” ከስምምነት ላይ መደረሱን አብራርተዋል።
“እንዲሁም ለዓመታት እየተንከባለሉ የመጡ የዳኞች፣ የሬጂስትራሮች፣ ሲቪል ሰራተኞች እና የጉባኤ ተሿሚዎች ጥያቄዎችም ቀስ በቀስ እንደሚፈቷቸውም ጭምር [በጊዜያዊ መስተዳድሩ ፕሬዝዳንት] ቃል የተገባበት ሂደት ነው ያለው” ሲሉም ከስምምነት ላይ የተደረሰበት ሌላ ጉዳይ ጠቅሰዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ከኃላፊነት ከስልጣን ለመልቀቅ “እንደ ምክንያት ያቀረቧቸው ጥያቄዎችን” በተመለከተ በውይይቱ “መተማመን ላይ እንደተደረሰ” ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያወጣው መግለጫ ያስረዳል።
መግለጫው፤ ከአመራሮቹ ጥያቄዎች ውስጥ “አንዳንዶቹ መልስ ስላገኙ፣ ሌሎቹም በሂደት መልስ እንደሚያገኙ በመረዳት ስራ፤ የመልቀቅ ጥያቄው ቀርቶ አመራሩ በስልጣኑ ላይ እንዲቀጥል መግባባት ላይ ተደርሷል” ሲል የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ አመራሮች ከስልጣን ለመልቀቅ የደረሱትን ውሳኔ መቀየራቸውን ገልጿል።
የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፀጋይ እና ምክትላቸው አቶ ገብረአምላክ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት “ተገቢ መልስ ስላገኙ ሁለቱም በስልጣናቸው እንደሚቆዩ” መግለጻቸውን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ መለስ ተናግረዋል።












