ፈረንሳይ ፍላጎት በመቀነሱ የወይን መጠጦችን ለማስወገድ 200 ሚሊዮን ዩሮ መደበች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፈረንሳይ መንግሥት የወይን መጠጦችን ለማስወገድና አምራቾችን ለመደገፍ 200 ሚሊዮን ዩሮ መደበ።
መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ሸማቾች ከወይን ይልቅ ቢራን ተመራጭ በማድረጋቸው እና በዘርፉ ጣፋጭ አልኮል መጠጦች ላይ ባጋጠመ ችግር የወይን መጠጥ ፍላጎት በመቀዛቀዙ ነው።
የፍላጎት እጦት ፣ የዋጋ ንረት እና የድኅረ ኮቪድ የምጣኔ ሃብት ቀውስ በአገሪቷ ባለው የወይን ምርት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል።
የወይን ምርቱ በገበያ ላይ ተፈላጊነቱ በመቀነሱም በአገሪቷ ያሉ ዋና ወይን አምራቾች ወጪያቸውን እንኳን መሸፈን ተስኗቸዋል።
ዘርፉን ለመደገፍም መጀመሪያ ላይ በአውሮፓ ኅብረት የተደረገው የ160 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ ወደ 200 ሚሊዮን ዩሮ እንዲያድግ ተደርጓል።
ከዚህ ውስጥም አብዛኛው ገንዘብ ከወይን ሻጮች ትርፍ ክምችት ለመግዛት የሚውል ሲሆን ከተበላሸው ወይን የሚገኘው አልኮልም የእጅ ማጽጃ ፣ ንጽህና መጠበቂያዎች እና ሽቶ ለሚያመርቱ ኩባንያዎች እንደሚሸጥ ተገልጿል።
ከዚህም ባሻገር ከመጠን በላይ ምርትን ለመቀነስ ወይን አምራቾች ምርቶቻቸውን እንደ ወይራ ባሉ ሌሎች ምርቶች እንዲለውጡም የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸዋል።
የግብርና ሚኒስትሩ ማርክ ፌስኖው፣ ገንዘቡን መመደብ ያስፈለገው የፈረንሳይ መንግሥት የዋጋ ግሽበትን ለማስቆም እና ወይን አምራቾች የገቢ ምንጭ እንዲያገኙ ለማስቻል በማለም እንደሆነ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም ምንም እንኳን ዘርፉን ለመደገፍ በርካታ ገንዘብ ቢመደብም የወይን ዘርፉን የወደፊት መጻኢ ዕድል መመልከት፣ የተጠቃሚዎችን ለውጦች መረዳት እና ከዚያ ጋርም መላመድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን መረጃ እንደሚያሳየው ሰኔ ወር ላይ የወይን መጠጥ ፍላጎት በጣሊያን 7 በመቶ፣ በስፔን 10 በመቶ ፣ በፈረንሳይ 15 በመቶ ፣ በጀርመን 22 በመቶ እና በፖርቹጋል 34 በመቶ ቀንሷል።
ይሁን እንጂ በዓለም ትልቅ ወይን አምራች በሆነው ቀጠናው ያለው የወይን ምርት 4 በመቶ አድጓል።












