የፓሪሱ ግድያ ተጠርጣሪ ከፍተኛ የሆነ የስደተኞች ጥላቻ እንዳለበት ለመርማሪዎች ተናገረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ የኩርድ ማኅበረሰብ ላይ ጥቃት አድርሶ ሰዎችን የገደለው ግለሰብ ለስደተኞች ከፍተኛ የሆነ ጥላቻ እንዳለው አመነ።
የፈረንሳይ አቃቤያነ ሕግ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት የ69 ዓመቱ ግለሰብ አርብ ዕለት ጥቃት መፈፀም ሲጀምር አውሮፓዊ ያልሆኑ የውጭ ዜጎችን ለመግደል እቅድ እንደነበረው ለመርማሪዎች ተናግሯል።
ተጠርጣሪው ግለሰብ በፖሊስ ከተጠየቀ በኋላም ወደ አዕምሮ ሕክምና እንዲገባ ተደርጓል።
በኩርዶች የባሕል ማዕከል ላይ ተኩስ ከፍቶ ሦስት ሰዎችን በመግደል ሌሎች ሦስት ሰዎችን ለጉዳት በመዳረግ ክስ ቀርቦበታል።
ዊሊያም ኤም የተባለው ተጠርጣሪ ጡረተኛው የባቡር አሽከርካሪ የነበረ ሲሆን እንደ አውሮፓውያኑ 2016 መኖሪያ ቤቱ ላይ ዘረፋ ከተፈፀመበት በኋላ ለድብርት እንደተጋለጠ እና ራስን የማጥፋት ስሜት እንዳደረበት ለፖሊስ መናገሩን የፓሪስ አቃቤያን እሁድ ዕለት ገልጸዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም ለውጭ ዜጎች ያለው ከፍተኛ ጥላቻ ወደ ስር መስደዱን ማመኑን በመግለጫው ተገልጿል።
መግለጫ እንዳመለከተው ዊሊያም አርብ ዕለት አውሮፓዊያን ያልሆኑትን ለመግደል በሰሜን ፓሪስ በብዛት ስደተኞች ወደሚገኙበት ሴንት ዴኒስ ነበር ያመራው። እዚያም ጥቂት ሰዎችን አገኘ።
ከዚያም ጥቃቱን ወደፈፀመበት ፓሪስ 10ኛ ዲስትሪክት አህመት ካያ የኩርዶች ማዕከል አምርቷል።
ዊሊያም በእነዚህ ማኅበረሰቦች ላይ ጥርሱን የነከሰው በሶሪያ ግጭት ውስጥ የተሳተፉ የኩርድ ታጣቂዎች ከእላሚክ ስቴት ጋር በነበራቸው ውጊያ እስረኞችን ከመግደል ይልቅ እስረኛ አድርገው ይዘዋል በሚል መሆኑን አቃቤያኑ ተናግረዋል።
ግለሰቡ በግድያ፣ በግድያ ሙከራ እና ድርጊቱን በዘረኝነት ተነሳስቶ በመፈፀም ወንጀል ተጠርጥሮም በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ጥቃት መፈፀሙን የግለሰቡ ማኅደር ያመለከተ ሲሆን የአርብ ዕለቱን ጥቃት ከመፈፀሙ ከቀናት በፊት በዋስ መለቀቁ ተገልጿል።
ባለፈው ዓመትም በዋና መዲናዋ በስደተኞች ካምፕ ላይ በዘረኝነት ተነሳስቶ በጎራዴ ጥቃት በመፈፀም ክስ ቀርቦበት ነበር።
አርብ ዕለት የፈፀመው ጥቃት በከተማዋ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።
ሰልፈኞች መንገድ ላይ እሳት በማቃጠል፣ ሕንጻዎች እና መኪናዎች ላይ ድንጋይ በመወርወር ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።
ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ኩርዶች ተጎጂዎችን ለማሰብ ዲ ላ ሪፐብሊክ በሰላም ከተሰባሰቡ በኋላ ነበር።
ከጥቃቱ በኋላ ኩርዶች የፈረንሳይ ባለሥልጣናት ጥበቃ እንዲያደርጉላቸው ጥሪ አቅርበዋል። የማኅበረሰቡ መሪዎችም ቅዳሜ እለት ከፓሪስ ፖሊስ አዛዥ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
የአርብ ዕለቱ ጥቃት የተፈፀመው እስካሁን ፍትሕ ባልተሰጠው ጥቃት ሦስት ኩርዳውያን ሴት የማኅበረሰብ አንቂዎች በዋና መዲናዋ ከተገደሉ ከአስር ዓመት በኋላ ነው።
በፈረንሳይ የኩርድሽ ዲሞክራሲያዊ ምክር ቤት (ሲዲኬ ኤፍ) ጠበቃ ማኅበረሰቡ እንደ አውሮፓውያኑ 2013 በተፈፀመው ጥቃት አሰቃቂ አጋጣሚን በማስተናገዱ አሁንም በድጋሜ ለስጋት ተዳርጓል ብለዋል።












