የሮሂንጋ ስደተኞች ለአንድ ወር ከእንጨት በተሠራች ጀልባ ባሕር ቀዝፈው ኢንዶኔዢያ ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በርካታ ቁጥር ያላቸው የሮሂንጋ ስደተኞች ሞተሯ በተበላሸች የእንጨት ጀልባ ቀዝፈው ኢንዶኔዢያ መድረሳቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ።
ሁሉም ወንዶች የሆኑት ስደተኞች ምዕራብ ኢንዶኔዢያ የባሕር ጠረፍ ሲደርሱ እጅግ ተዳክመው እና ተርበው ነበር ተብሏል።
ከስደተኞቹ መካከል ቢያንስ ሦስቱ ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።
በትውልድ አገራቸው ማይናማር ወይም በርማ አናሳ ቁጥር ያላቸው ሮሂንጋዎች፤ ዜግነት ከመከልከል ባፈ የተገፉ ሕዝቦች ናቸው።
57 ሰዎችን ያሳፈረችው ጀልባ ምዕራብ ኢንዶኒዢያ በምትገኝ አኬህ ግዛት መድረሷን የፖሊስ ቃል አቀባይ ዊናርዳይ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል
“የጀልባዋ ሞተር ተበላሽቶ የነበረ ሲሆን ወደ ጠረፍ የመጣችው በንፋስ ተገፍታ ነው” ብለዋል የፖሊስ ቃል አቀባዩ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ስደተኞቹ በባሕሩ ላይ ለወር ያህል ሲቀዝፉ መቆየታቸውን መናገራቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
አንድ የአገሪቱ የኢሚግሬሽን ባለስልጣን ለኤኤፍፒ ሲናገሩ ስደተኞቹ በግዚያዊነት በመንግሥት መጠለያ ጣቢያ እንዲቆዩ ይደረጋሉ።
ቁጥራቸውን 58 የሚደረሱት ስደተኞች መነሻቸው ከየት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት 150 የሮሂንጋ ስደተኞች ከባንግላዴሽ ከተነሱ በኋላ ባሕር ላይ መሄጃ ጠፍቷቸው ያሉበት አልታወቀም ተብሎ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ሳምንት በደቡብ ምስራቅ እስያ አዳማና ባሕር ላይ 150 ስደተኞችን ጭና ጉዞ የጀመረችውን አሳ ማጥመጃ ጀልባ አፈላልገው እንዲረዱ በባሕሩ ዙሪያ የሚገኙ አገራትን አሳስቦ ነበር።
ባሕር ላይ የነበሩት ሰዎችን በሳተላይት ስልክ አማካይነት ማግኘት ተችሎ የነበረ ሲሆን በወቅቱ ሕጻናትን ጨምሮ ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ምግብ እና የመጠጥ ውሃ መጨረሳቸውን ተናግረው ነበር።
ተመድ እነዚህን ስደተኞች የጫነችው ጀልባ ሳትሰጥም አትቀርም ሲል ትናንት እሁድ ስጋቱን ገልጿል።
እአአ 2017 ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው የሮሂንጋ ሙስሊሞች በማይናማር መንግሥት ጦር የተከፈተባቸውን የዘር ማጥፋት በመሸሽ ባንግላዴሽ ገብተው ነበር።
በቅርብ ወራት ደግሞ ከተጨናነቁት የባንግላዴሽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ለመውጣት በሚል አደገኛ የሆኑ የባሕር ላይ ጉዞዎችን እያደረጉ ይገኛሉ።
በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ያለው አስከፊ ሁኔታ እየጨመረ በመምጣቱ መጠለያ ጣቢያውን ጥለው የሚሸሹ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።
በሌላ በኩል በትውልድ አገራቸው ማይናማር የሚገኙ ስደተኞችም የአገሪቱ ጦር መፈንቅለ መንግሥት ማድረጉን ተከትሎ አገር ጥለው እየሸሹ ነው።
እስካሁን ቢያንስ አምስት ጀልባዎች ባለፉት ሁለት ወራት ከማይናማር ስደተኞችን ይዘው ተነስተዋል።












